የንግድ እቃዎች ዘካት

4391

   የንግድ እቃዎች ትርጓሜ

የንግድ እቃዎች

የንግድ እቃ ለማትረፍ ተብሎ ለሸያጭና ለግዥ የተዘጋጀ ማንኛውም ነገር ነው፡፡

   የንግድ እቃ ለእይታ ቀርቦ ከዚያ የሚያልፍ በመሆኑና ቋሚ ባለመሆኑ ነው ‹‹ዑሩድ አት’ትጃራ›› ተብሎ የተሰየመው፡፡ ነጋዴው እነዚህን ሻቀጦች የሚፈልጋቸው ለሸቀጥነታቸው ሳይሆን ወደ ገንዘብ ለውጦ ለሚያገኘው ትርፍ ሲል ነው፡፡

   የንግድ ሸቀጥ እንደ መኪናዎች፣አልባሳት፣ጨርቃጨርቆች፣ብረታብረት፣እንጨትና የመሳሰሉ ለንግድ ልውውጥ የተዘጋጁ ነገሮችን የሚያጠቃልል ከጥሬ ገንዘብ ውጭ ያለ ሁሉም የሀብት ዓይነት ነው፡፡

   አልባሳት
   መኪና
   እንጨት
   ብረት

   የንግድ እቃዎች ዘካትን የሚመለከት ድንጋጌ

   በንግድ እቃዎች ላይ ዘካ መክፈል ግዴታ ነው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏልና ፡- ‹‹እላንተ ያመናችሁ ሆይ! ካፈራችሁትና ከዚያም ለናንተ ከምድር ካወጣንላችሁ ከመልካሙ ለግሱ፤››[አል-በቀራህ፡267]

   ሁሉም የዕውቀት ባለቤቶች በዚህ አንቀጽ ማለት የተፈለገው የንግድ እቃ ዘካት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም አላህ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹ከገንዘቦቻቸው ስትሆን በርሷ የምታጠራቸው እና የምታፋፋቸው የሆነችን ምጽዋት ያዝ፤›› [አል-ተውባህ፡103]

   የንግድ ገንዘብ ከገንዘብ ሁሉ ይበልጥ የጎላ በመሆኑ ዘካት ዋጅብ ሆኖበታል፡፡

   የንግድ እቃዎች ዘካት ግዴታ እንዲሆን መሟላት ያለባቸው ቅድመ ሸርጦች

   1 - የንብረቱ ዋጋ ለዘካት መክፈያ መጠን (ንሷብ) የደረሰ መሆን፡፡ ንሷብ በወርቅና ብር ዋጋ ተመን ይሰላል፡፡

   2 - አንድ ዓመት የሞላው መሆን፡፡

   3 - ለንግድ ዓለማ፣ለሥራና ለትርፍ ማግኛነት የተዘጋጀ መሆን፡፡ ነቢዩ ﷺ ‹‹ሥራዎች (የሚለኩት ከጀርባቸው ባለው ቁርጠኛ) ውሳኔ ነው፤እያንዳንዱ ሰውም በንይ’ያው መሰረት ነው የሚያገኘው፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

   ሃሳቡንና ዓላማውን ከንግድነት ወደ ግል ፍጆታነት ከለወጠው የዓመት መሙያው ይቋረጣል፡፡ ኒያውን እንደገና ወደ ንግድ ከመለሰው ደግሞ ዓመቱ እንደ አዲስ መቆጠር ይጀምራል፡፡ ያቋረጠው ዓመቱ እንዳይሞላ በማድረግ ከዘካት ክፍያ ለማምለጥ የፈጸመው አሻጥር ከሆነ ግን የዓመት ቆጠራው አይቋረጥም፡፡

   ምሳሌ፡ በሙሐረም ወር ለንግድ ዓላማ ብሎ መሬት ቢገዛና በኋላ ሸዕባን ወር ላይ ሀሳቡን መኖሪያ ቤት ወደ መስራት ቢቀይር የዓመት ቆጠራው ይቋረጣል፡፡ ከዚያም በሸዋል ወር ወደ ንግድ ሃሳቡ እንደገና ቢመለስ የአዲስ ዓመት ቆጠራው የሚጀምረው ከሸዋል ይሆናል፡፡ ያንን ያደረገው ከዘካት ክፍያ ለማምለጥ አስቦ ከሆነ ግን የዓመት ቆጠራው አይቋረጥም፡፡

   የንግድ ሸቀጦች ዘካት እንዴት እንደሚከፈል

   ዓመት ከሞላው ሸቀጦቹ ተለይተው ዛሬ ባለው የገበያ ዋጋቸው ይተመኑና ዘካው ከእቃዎቹ ላይ በዓይነት ወይም ለተቀባዩ ይበልጥ ጠቃሚ ከሆነ ከዋጋቸው ላይ ተሰልቶ ይከፈላል፡፡

   የንግድ ሸቀጦች ዘካን ሂሳብ ነጋዴው እንዴት ያሰላል ?

   1 - ያለው የንግድ ሸቀጥ ሁሉ ዛሬ ባለው የገበያ ዋጋ ይተመናል፡፡

   2 - ያለውን ጥሬ ገንዘብ ሁሉ ለንግድ የተጠቀመበትም ይሁን ያልተጠቀመበትን ከሸቀጡ ሂሳብ ላይ ይጨምራል፡፡

   3 - በሰው ላይ ያለውንና እንደሚከፈለው እርግጠኛ የሆነውን የሚሰበሰብ ብድርም ይጨምርበታል፡፡

   4 - ከዚህ ጠቅላላ ድምር ላይ በርሱ ላይ ያለውን የሌሎችን እዳ ሁሉ ይቀንሳል፡፡

   5 - በቀረው ጠቅላላ ድምር ላይ የአንድ አስረኛ ሩብ (2 .5%) አስልቶ ዘካትውን ይከፍላል፡፡

   ግዴታ የሆነው ዘካት = (የሸቀጦች ዋጋ ተመን + ጥሬ ገንዘብ + በሌሎች ላይ ያለው ሊሰበሰብ ሚችል ብድር -- በርሱ ላይ ያለው የሌሎች ዕዳ) × (የዘካት መክፈያ ምጣኔ 2 .5% በጨረቃ አቆጣጠር አንድ ዓመት)፡፡

   - የንግድ ዘካን ለማስላት ዘካት የሚከፈልበት ዕቃ ተለይቶ ቆጠራ ይደረግና ዘካው ዋጅብ በሆነበት ዕለት የገበያ ዋጋ በማእከላዊው የፋይናንስ ተቋም የዋጋ ዝርዝር በመታገዝ የተቆጠረው እቃ ሂሳብ ይሰላል፡፡ ይህ ሂሳብ የትርፍና ኪሳራን ነገር በጭራሽ ግምት ውስጥ አያስገባም፡፡

   - ለማሸጊያነትና ለመጠቅለያነት የዋሉ ቁሳቁሶች በራሳቸው ለመልሶ ሽያጭ ዓላማ በተናጠል የተገዙ ካልሆኑ በስተቀር በተለይ አይታሰቡም፡፡ ልዩ ዓይነት ከረጢቶችና ኪሶችን የመሳሰሉ ለንግድ እቃው ሽያጭ አገልግሎት የሚውሉ ሆነው የእቃዎቹን ዋጋ ከፍ የሚያደርጉ ከሆኑ ይታሰባሉ፡፡ የመጥቅለያ ወረቀቶችን የመሳሰሉና በዋጋ ላይ ጭማሪ የማያመጡ ከሆኑ ግን ሂሳብ ውስጥ አይገቡም፡፡

   - ቆጠራና ሂሳቡ ለያንዳንዱ ነጋዴ፣ለጅምላ ነጋዴውም ለቸርቻሪውም ሲሆን፣የሚተመነው በተለምዶ በዓመቱ መጨረሻ ላይ ለመግዛት በሚቻለው ዋጋ - የመተኪያ ዋጋ - ነው፡፡ ይህም ከመሸጫ ዋጋ - የገበያ ዋጋ - እና ከመግዣ ወጭ ይለያል፡፡

   - ዘካው በነጋዴው ላይ በጸናበት ቀንና ዘካው በተከፈለበት ቀን መካከል የዋጋ ለውጥ ከተከሰተ፣ዋጋው ጨመረም ቀነሰ ግምት ውስጥ የሚገባው ግዴታው በጸናበት ቀን የነበረው ዋጋ ነው፡፡

   - በመጓጓዝ ላይ የሚገኝ የንግድ እቃ ርክክብ ከመከናወኑ በፊት ዘካው በባለቤቱ ላይ ነው፡፡ በተገዛ እቃ ላይ ባለቤት የሚኮነው በሰነዱ ላይ በሰፈረው የርክክብ ዓይነት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል እቃው የተገዛው በሻጩ ወደብ ላይ በሚፈጸም ርክክብ መሰረት ከሆነ አጓኋዡ እቃውን ለመጫን ሲረከብ ባለቤትነቱ በቀጥታ ወደ ገዥው ይተላለፋል፡፡ እቃው የተገዛው በገዥው ወደብ ላይ በሚፈጸም ርክክብ መሰረት ከሆነ ወደ መድረሻው ወደብ ሲደርስ ነው ወደ ገዥው ባለቤትነት ስር የሚገባው፡፡

   - የንግድ ገንዘቡ የተለያዩ የመገበያያ ገንዘቦችን (ከረንሲ)፣ ወርቅ ወይም ብርን የሚያጠቃልል ከሆነ፣መከፈል የሚገባውን መጠን ለማወቅ ነጋዴው የንግድ እቃውን ሂሳብ ለማስላት በተጠቀመበት የመገበያያ ገንዘብ መሰረት ዘካው ዋጅብ በሆነበት ቀን በነበረው ዋጋ ያሰላል፡፡

   - ገዥ ዋጋውን ወደፊት ለመክፈል ተሳማምቶ የገዛውና ገና ያልተረከበው የንግድ እቃ ዋጋ ዘካት የሚጸናው በገዥው ላይ ሳይሆን በሻጩ ላይ ነው፡፡

   ለማምረቻ እንዱስትሪ የሚውሉ ጥሬ እቃዎችና አጋዥ ግብዓቶች ዘካት

   1 - በመኪና እንዱስትሪ እንደ ብረታብረት ያለው፣በሳሙና እንዱስትሪ እንደ ዘይት ያሉና ለሚመረተው እቃ በመጀመሪያ ደረጃ ግብዓትነት የሚያገለግሉ ጥሬ እቃዎች በዓመቱ መጨረሻ ሊገዙ በሚችሉበት ዋጋቸው መሰረት ዘካት ይከፈልባቸዋል፡፡ ይህ ለፋብሪካ ግብዓትነት የሚውሉ እንስሳትን፣እህልና እጸዋትን የመሳሰሉትን ሁሉ ያካትታል፡፡

   2 - በቀጥታ ወደሚመረተው እቃ የማይገቡ እንደ ነዳጅ ያሉት አጋዥ እቃዎች እንደ ቋሚ ንብረቶች ሁሉ ዘካ አይከፈልባቸውም፡፡

   3 - ያልተፈበረኩ እቃዎችና ምርታቸው ገና ያልተጠናቀቀ እቃዎች ዘካት ፡-

   - ዘካት የፋብሪካ ውጤት ባልሆኑትና ተፈብርከው ገና ባልተጠናቀቁ እቃዎች ላይ ባሉበት ሁኔታ በሚያወጡት ዋጋ መሰረት በዓመቱ መጨረሻ ላይ በንግድ ሸቀጦች ዘካት ሂሳብ መሰረት ይከፈልባቸዋል፡፡

   ከንግድ እቃዎች ጋር ተጨማሪ የሆነ የዘካት ምክንያት መኖር

   - እንደ እርሻ ውጤቶች ያለ ተጨማሪ የሆነ የዘካት ምክንያት ከንግድ እቃዎች ጋር ሲኖር ልክ እንደ ንግድ እቃዎች ዘካት ይከፈልባቸዋል፡፡ [ዶክተር ሰላሕ አስ’ሳዊ ቀዷያ ፍቅህይያ ሙዓስራ ገጽ 51 እና ቀጥሎ ያለው፡፡]

   ዘካት ግዴታ የማይሆንባቸው የሀብት ዓይነቶች

   - እንደ እንቁ፣የከበሩ ድንጋዮችና ዓሳ ያሉ ከባሕር የሚወጡ ነገሮች ወደ ንግድ ሸቀጥነት እስካልተለወጡ ድረስ የዘካ ግዴታ የለባቸውም፡፡

   - እንደ ሪል እስቴት ያሉ ለክራይ የተዘጋጁ ቤቶችና መኪናዎችን የመሳሰሉት ዓመት ሲሞላቸውና ንሷብ ሲደርሱ በሚያስገኙት ገቢ ላይ እንጂ በራሳቸው በንብረቶቹ ላይ ዘካት አይከፈልም፡፡

   - ለመሰረታዊ አገልግሎቱ ሰው የሚጠቀምባቸው መኖሪያ ቤትና የቤት መኪናን የመሳሰሉ ንብረቶች ዘካት የለባቸውም፡፡

   በካፒታል ላይ የሚከፈል ዘካት
   ከንግድ ሸቀጥ ዘካት የሚከፈልበት ለትርፍ ዓላማ ለሽያጭና ለግዥ ልውውጥ የሚዘጋጀው ራስማል (ካፒታል) ነው፡፡ ቋሚ የሆነ ንብረት ግን ዘካት ለማውጣት በሚደረገው ሂሳብ ውስጥ አይገባም፣ዘካም አይከፈልበትም፡፡ እነዚህም እንደ መደርደሪያዎች፣ የሸቀጥ ማቆያ ማቀዝቀዣዎች፣ ሸቀጦቹን ለማመላለስ የሚያገለግሉ ተሸከርካሪዎች፣የእቃ ማንሻ መሳሪያዎችና የመሳሰሉት ናቸው፡
   የንሷብ መጠን ባለቤትነት

   ዓመቱን በሙሉ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ድረስ ገንዘቡ የዘካት ማስከፈያ ንሷብ መሙላት እንደ ቅድመ ሁኔታ ይቀመጣል? ወይስ በዓመቱ መጀመሪያና በዓመቱ መጨረሻ ብቻ ንሷብ የሞላ መሆኑ በቂ ይሆናል ?

   ዓመቱን በሙሉ ሂሳቡን ማስላትና መተመን አስቸጋሪ በመሆኑ፣ግምት ውስጥ የሚገባው በዓመቱ መጀመሪያና መጨረሻ ንሷብ የሞላ መሆኑ ነው፡፡ የዓመቱ መጀመሪያ ግምት ውስጥ የሚገባው የግዴታነቱ ምክንያት በመፈጠሩ ሲሆን የዓመቱ መጨረሻ ደግሞ የመክፈያ ጊዜው በመድረሱ ነው፡፡ አንድ ሙስሊም ግለሰብ ገንዘቡን አስቦና ተምኖ ዘካ የሚያወጣበትን እንደ ወርሐ ረመዷን ወይም ሌላ ወር ያለ የተወሰነ የጊዜ ቀጠሮ መያዙ ነገሩን የበለጠ ያመቻችለታል፡፡

   የአክሲዮን እጣ ዘካት

   የአክሲዮን እጣ ትርጓሜ

የአክሲዮን እጣ

የአክሲዮን እጣ የአክሲዮን ኩባንያ ካፒታል እኩል ከሆኑ እጣዎች አንዱ እጣ ነው፡፡

  ምሳሌ፡ ዋና ካፒታሉ ሦስት ሚሊዮን ዶላር የሆነ የአክስዮን ማህበር ኩባንያ ሲመሰረት ካፒታሉን እያንዳንዳቸው 300 ዶላር በሆኑ አስር ሺህ እጣዎች ከፋፈለ፡፡ ይህ አንድ ክፍልፋይ እጣ ነው የአክሲዮን አንድ እጣ የሚባለው፡፡ የእጣው ባለቤትም በያዛቸው እጣዎች ልክ የኩባንያው ባለአክሲዮን ሸሪክ ነው፡፡

  የአክሲዮን እጣ ዘካት ግብይትን የሚመለከት ድንጋጌ

  የኩባንያው የሥራ መስክ ሐራም እስካልሆነ ወይም በአራጣ የሚሰራበት ሁኔታ እስካልኖረ ድረስ ግብይቱ የተፈቀደ (ጃእዝ) ነው፡፡

  የአክሲዮን እጣ ዘካት አወጣጥ

  - በኩባንያው መተዳደሪያ ደንብ ውስጥ የተደነገገ ከሆነ ወይም ባለ አክሲዮኑ ውክልና ከሰጠው፣የኩባንያው ሥራ አመራር ዘካውን ያወጣል፡፡

  - ኩባንያው ዘካት የማውጣቱን ኃላፊነት ከወሰደ የእስላማዊ ኮንፈረንስ ድርጅት አካል የሆነው እስላማዊ የፍቅህ አካዳሚ የቤት እንስሳትን ዘካ አስመልክቶ በሱና ውስጥ የተጠቀሰውንና አንዳንድ ፉቀሃእ ሁሉንም የዘካ ዓይነት የሚያጠቃልል አድርገው የሚወስዱትን የመቀየጥ መርህን በመመርኮዝ ዘካውን ሕጋዊ ሰውነት ያለው አድርጎ ይወስደዋል፡፡ ይህም የሁሉን ባለ አክስዮኖች ገንዘብ እንደ አንድ ግለሰብ ንብረት አድርጎ በመቁጠር ንሷቡንም ሆነ መጠኑን ከዚህ አኳያ ማስላት ነው፡፡

  - ብዙኃኑ የዕውቀት ባለቤቶች ግን የኩባንያዎችን ዘካት በተመለከተ መፈጸም ያለበት የመቀየጥ መርህ ሳይሆን የያንዳንዱን ባለ አክስዮን እጣ ግምት ውስጥ በማስገባት መሆን አለበት የሚል አቋም አላቸው፡፡

  እዚህ ላይ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ የእሰላማዊ ጥናትና ምርምር አካዳሚ ሁለተኛ ጉባኤ በዚህ ጉዳይ ላይ የብዛኃኑን ፉቀሃእ አቋም በመከተልና የመቀየጥን መርህ ወደ ጎን በመተው፣የያንዳንዱን ባለ አክስዮን እጣ ግምት ውስጥ አስገብቶ የሚከተለውን የወሰነ መሆኑ ነው ፡-

  ‹‹በርካታ ግለሰቦች በአክስዮን ባለቤትነት በሚሳተፉባቸው ኩባንያዎች ውስጥ እነዚህን ድንጋጌዎች በመተግበሩ ረገድ ግምት ውስጥ መግባት ያለበት የኩባንያዎቹ ጠቅላላ ትርፍ ሳይሆን የያንዳንዱ ባለ አክስዮን ትርፍ በተናጠል መሆን ይኖርበታል፡፡››

  - በዚህ ሁኔታ የኩባንያው ሥራ አስፈጻሚ ከካፒታሉ ላይ የዘካት ግዴታ የማይመለከታቸውንና እንደ ወቅፍ ተቋሞች፣የግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣በጎ አድራጊ ወገኖች ባሉት የተያዙ አክስዮኖችን፤እንደዚሁም እንደ ሕንጸዎች፣ቢሮዎች፣የቢሮ እቃዎችና መገልገያ መኪኖችና የመሳሰሉትን ዘካት የማይከፈልባቸውን የኩባንያውን ቋሚ ንብረቶች ከካፒታሉ መቀነስ ይኖርበታል፡፡

  የኩባንያው ሥራ አመራር ዘካውን ያላወጣ ከሆነ ግን ባለ አክስዮኖቹ ራሳቸው በሚከተለው ሁኔታ ዘካውን የማውጣት ግዴታ ይኖርባቸዋል ፡-

  1 - የእርሻና ግብርና ኩባንያዎች አክሲዮን በእህል ሰብልና በፍራፍሬ ዘካት ውስጥ በተመለከተው መሰረት ዘካው ይከፈላል፡፡

  2 - የንግድ ሥራ ኩባንያዎች አክስዮን ዘካው ከዋናው ገንዘብና ከትርፉም አንድ ላይ የሚከፈል ሲሆን፣የአክስዮን እጣዎቹ ተመን ዘካው ዋጅብ በሆነበት ዕለት በነበረው የገበያ ዋጋ መሰረት ይሰላል፡፡

  3 - የፋብሪካና እንዱስተሪ አክስዮኖች ዘካት የሚወጣው ከማምረቻ መሳሪያዎቹ፣ከሕንጻዎቹና ከመሳሰሉት ሳይሆን ከተጣራ ትርፉ ነው፡፡

  4 - አንድ ባለ አክሲዮን እጣውን በዓመቱ ውስጥ ቢሸጥ ዋጋውን ከሌላው ገንዘቡ ጋር ይጨምርና የዘካት መክፈያ ዓመቱ ሲሞላ አንድ ላይ ዘካውን ያወጣል፡፡ ገዥው ደግሞ ከላይ በተዘረዘረው መሰረት ዘካውን ይከፍላል፡፡ [ዶክተር ሰላሕ አስ’ሳዊ ቀዷያ ፍቅህይያ ሙዓስራ ገጽ 54 እና ቀጥሎ ያለው፡፡]