የግዴታውን ዓይነት በተመለከተ
በሚከፈለው ዘካት ግዴታው ከመካከለኛው ዓይነትና ጥራት መሆን እንጂ ከምርጡ ወይም ከመናኛው ዓይነት አለመሆን ነው፡፡ ዘካት ሰብሳቢው ከተደነገገው እድሜ በታች የሆነ እንስሳ ለዘካ መቀበል የድሆችን ጥቅም የሚጎዳ በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡ ከዕድሜ በላይ የሆነውን መቀበልም ፍትሕ ማጓደል በመሆኑ መጠንቀቅ ይኖርበታል፡፡
የታመመ፣እንከን ያለበትና ያረጀ እንስሳ ድሆችን ስለማይጠቅም መቀበል የለበትም፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ለእርድ የሰባውን ሙክት፣የሚያጠቡትንና እርጉዞችን፣ቀልብ የሚስቡ ውድና ምርጥ እንስሳትን መውሰድ ሀብታሙን መጉዳት ስለሚሆን መደረግ የለበትም፡፡ የአላህ መልእክተኛ ﷺ ‹‹ውድና ተመራጭ ገንዘባቸውን ከመውሰድ ተጠንቀቅ፡፡› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡
የቤት እንስሳት ቅየጣን በተመለከተ
ቅየጣ ሁለት ዓይነት ነው ፡-
አንደኛው ዓይነት ፡ የዓይነት ቅየጣ
ይህ ንብረቱ የሁለት ግለሰቦች የጋራ ንብረት ሆኖ ያንደኛቸው ድርሻ ከሌላኛው ድርሻ ተለይቶ የማይታወቅበት ሁኔታ ነው፡፡ የዓይነት ቅየጣ በውርስ ወይም በግዥ ምክንያት ሊፈጠር ይችላል፡፡
ሁለተኛው ዓይነት ፡ የቅርርብ ቅየጣ
ይህ ደግሞ የያንዳንዳቸው ድርሻ ተለይቶ የሚታወቅ ሆኖ ቅርበትና ጉርብትና ሲያገናኛቸው ነው፡፡
በሁለቱም ዓይነት ቅየጣው የሁለቱ ንብረቶች ድምር ንሷብ የሚሞላና ሁለቱም የዘካት ግዴታ የሚጸናባቸው ከሆነ እንደ አንድ ንብረት ይቆጠራሉ፡፡ አንዳቸው ዘካት የማይከፍል ካፍር ቢሆን ቅየጣው ትክክለኛ ያልሆነና ምንም ውጤት የማይኖረው ይሆናል፡፡
የተቀላቀሉት ንብረቶች መጠለያና ማደሪያን የሚጋሩ፣በመሰማራትና በመመለስ፣በመታለብ፣ በግጦሽና በሚያጠቃ ኮርማም ጭምር የሚጋሩ መሆን ይኖርባቸዋል፡ አነዚህ ቅድመ ግዴታዎች ከተሟሉ ሁለቱ ንበረቶች በቅየጣው ውጤት እንደ አንድ ንብረት ይወሰዳሉ፡፡
ነቢዩ ﷺ ‹‹የዘካት ክፍያን በመፍራት የተለያው (ንብረት) አንድ ላይ አይሆንም፣አንድ ላይ የሆነውም አይለያይም፡፡ የተቀላቀለ የጋራ ንብረት ያላቸው (የቅልቅሉን ውጤት) እኩል ይጋራሉ፡፡፡›› [በእብን ኹዘይማ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡ መቀላቀል በተለይ የቤት እንስሳትን በተመለከተ ብቻ ዘካን ግዴታ ሊያደርግና ውድቅም ሊያደርግ ይችላል፡፡
የተለያዩትን አንድ ላይ የመቀላቀል ምሳሌ፡ ሦስት ግለሰቦች እንዳንዳቸው አርባ በድምሩ መቶ ሃያ በጎች አሏቸው፡፡ በጎቹን እንደ አንድ ንብረት አንድ ላይ ብንቀላቅል ግን የዘካት ግዴታው አንድ ፍየል ብቻ ይሆናል፡፡ እያንዳንዳቸውን በተናጠል ብንወስድ ግን ለየአርባው ሦስት ፍየሎችን መክፈል ግዴታ ይሆንባቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም መክፈል ያለባቸው የዘካት ግዴታ ሦስት ፍየሎች ሳይሆን አንድ ፍየል ብቻ እንዲሆንላቸው አንድ ላይ ቀላቀሉ ማለት ነው፡፡
አንድ ላይ የሆኑትን የመለያየት ምሳሌ፡ አንድ ግለሰብ አርባ በጎች እያሉት ዘካ ሰብሳቢ መምጣቱን ሲያውቅ በጎቹን ይለያያቸውና ሃያውን አንድ ቦታ ቀሪዎቹን ሃያ ደግሞ ሌላ ቦታ ያደርጋል፡፡ በዚህም ተለያይተው ከአርባ በታች ስለሆኑና ንሷብ ስለማይሞሉ ከዘካት ያመልጣል፣አይከፍልም ማለት ነው፡፡