ኢማምነትና ኢማምን መከተል

3303

    ለኢማምነት ይበልጥ የተገባ ሰው

    በዚህ ቅደም ተከተል መሰረት ይሆናል፡-

    አንደኛ ፡- የአላህን መጽሐፍ (ቁርኣንን) ይበልጥ የቀራ፤ይህም ከቀረቡት መካከል ቁርኣንን ይበልጥ በቃሉ የሚያውቅ (ሓፍዝ) እና ስለ ሕግጋቱ የበለጠ ዕውቀትና ግንዛቤ ያለው ነው፡፡

    ሁለተኛ ፡- የነቢዩን ﷺ ሱንና የበለጠ የሚያውቅ፤ይህ ደግሞ ትርጉሙንና ዝርዝር ድንጋጌዎቹን ይበልጥ ሚያውቅ ሰው ነው፡፡

    ሦስተኛ ፡- በህጅራ (ስደት) ቀዳሚ የሆነ፤ይህ ከክህደት አገር ወደ እስላም አገር በመሰደድ ቅድሚያ ያለው ሲሆን፣የዚህ ዓይነቱ ህጅራ በማይኖርበት ሁኔታ ተውበት በማድረግና ኃጢአቶችን ጥሎና ተጸጽቶ በመሰደድ ቀዳሚ የሆነ ሰው ነው፡፡

    አራተኛ ፡- በዕድሜ የሚበልጥ፤ይኸኛው መመዘኛ የሚመጣው ከላይ በተዘረዘሩት ሁሉም እኩል በሚሆኑበት ጊዜ ነው፡፡

    ለዚህ ሁሉ ማስረጃው ቀጣዩ ሐዲስ ነው፡፡ ከአቡ መስዑድ አልአንሷሪ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት የአላህ መልእክተኛ ﷺ ፡‹‹ሰዎችን በኢማምነት የሚመራው ከመካከላቸው ይበልጥ የአላህን መጽሐፍ የቀራው ነው፡፡ በቅራኣው እኩል ከሆኑ ሱንናን ይበልጥ የሚያውቀው ነው፡፡ በሱንናም እኩል ከሆኑ በህጅራ ቀዳሚው ነው፡፡ በህጅራ እኩል ከሆኑ በመስለም [በሌላ ዘገባ በዕድሜ የሚል ተመልክቷል፡፡] የሚቀድመው ነው፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ለዚህ ቅደም ተከተል ትኩረት የሚሰጠው ለአንድ መስጊድ ወይም መደበኛ ኢማም ለሌላቸው ጀማዓ ኢማም መመደብ ሲፈለግ ነው፡፡ ጀማዓው መደበኛ ኢማም ካለው፣ኢማሙ የቤቱ ባለቤት ወይም በቦታው የማዘዝ ሥልጣን [በየቦታው ሹም፣መሪ ወይም አስተዳዳሪና የመሳሰለው መሆን፡፡] ያለው ሰው በሚሆንበት ጊዜ ግን ከሌሎች ይልቅ እራሱ ቀዳሚ ይሆናል፡፡

    ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹አንድ ሰው ለሌላው ሰው ሥልጣኑ ስር ባለው ቦታ ኢማሙ አይሁን፤ከርሱ ፈቃድ ወጭም በቤቱ የእንግዳ ማስቀመጫ ቦታው ላይም አይቀመጥ፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    የኢማሙና የተከታዮች መቆሚያ ቦታ

    1 - ተከትሎ የሚሰግደው መእሙም አንድ ብቻ ከሆነ ከኢማሙ በስተቀኝ አጠገቡ መቆም ሱንና ነው፡፡ እብን ዐባስ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት፡- ‹‹አንድ ሌሊት ከነቢዩ ﷺ ጋር ለመሰገድ በስተግራቸው ስቆም፣የአላህ መልእክተኛ ﷺ ከኋላዬ ራሴን ይዘው በቀኛቸው በኩል አደረጉኝ፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    2 - ጀማዓው ሁለትና ከዚያ በላ ከሆነ ኢማሙ ከረድፉ ፊትለፊት መሀል ላይ ይቆማል፡፡ ጃቢር (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ፡- አንደኛቸው ከአላህ መልእክተኛ ﷺ በስተቀኝ ቆመ፤ሌላኛው ደግሞ በስተግራቸው፡፡ ‹‹የአላህ መልእክተኛ ﷺ ሁላችንንም እጆቻችንን በመያዝ ከኋላቸው እስካቆሙን ደረስ ገፉን፡፡›› [በሙስሊም ተዘገበ] ብለዋል፡፡

    3 - የሶፍ ሞልቶ መቆሚያ ማጣትን የመሳሰለ በቂ ምክንያት ሳይኖር ከሶፍ በኋላ ለብቻው የሚሰግድ ሰው፣ሶላቱ ትክክለኛ አይሆንም፡፡

    የሴቶች መቆሚያ ቦታ

    1 - ሴቶች በጀማዓ ከሰገዱ ኢማሟ በሶፋቸው መሀል ከነሱ እኩል መቆምና ከፊትለታቸው አለመሆን ሱንና ነው፡፡

    2 - ከአንድ ወንድ ጋር ከሰገደች ከጀርባው ትቆማለች፣ከብዙ ወንዶች ጋር ከሰገደች ከሶፉ ኋላ ትቆማለች፡፡

    3 - ብዙ ሴቶች ከወንዶች ጋር ጀማዓ ከሰገዱ ከወንዶች ኋላ በኩል ቀረት ብለው ሶፋቸው እንደ ወንዶቹ ሶፍ መሆኑ ሱንና ነው፡፡ ከአቡ ሁረይራ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት የአላህ መልእክተኛ ﷺ ፡- ‹‹በላጩ የሴቶች ሶፍ የመጨረሻው ነው፤መጥፎው ደግሞ የመጀመሪያው ነው፡፡›› [በእብን ማጃህ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    የሴቶች ሶላት
    ሴት በወንዱ ጎን

    ኢማምን ተከትሎ መስገድን ከሚመለከቱ ድንጋጌዎች

    1 - አንድ ሰው እቤቱ ሆኖ በድምጽ ማጉያ ወይም በሬዲዮ አማካይነት የኢማሙን ድምጽ እየሰማ መከተል ትክክል አይደለም፡፡

    2 - ሶፉ የተያያዘ እስከ ሆነ ድረስ ከመስጊድ ውጭ ሆኖ ኢማሙን ተከትሎ መስገድ ትክክለኛ ነው፡፡

    3 - የኢማሙን ድምጽ እስከ ሰሙ ድረስ መእሙሞች ከመስጊዱ ጣሪያ ላይ ወይም በምድር ቤቱ ሆነው ተከትለው መስገድም ትክክለኛ ነው፡፡

    4 - የግዴታ ሶላት የሚሰግድ ሰው ሱንና በሚሰግድ ሰው ኢማምነት መስገድና ተቃራኒውም ትክክለኛ ነው፡፡ ለምሳሌ ያመለጠውን የጀማዓ ሶላት አጅር ለማግኘት ተራዊሕ የሚሰግድ ኢማምን ተከትሎ የዕሻን ፈርድ ሶላትን መስገድ ትክክለኛ ነው፡፡ ከጃቢር ብን ዐብደላህ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት፡- ‹‹ሙዓዝ ከነቢዩ ﷺ ጋር ይሰግዱና ወደ ሰዎቻቸው (መንደራቸው) መጥተው ያሰግዷቸው ነበር፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ከመስጊድ ውጭ ሆኖ ኢማሙን ተከትሎ መስገድ

    ኢማሙን መቅደም

    1 - መእሙም (ኢማምን የሚከተል ሰጋጅ) አንድን የሶላት ክንዋኔ ኢማሙን ተከትሎ ወዲያው በመፈጸም በርሱ መመራት የተደነገገ ነው፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹ኢማም የተደረገው ሊመሩበት ነው ነውና አል’ሏሁ አክበር ሲል አል’ሏሁ አክበር በሉ፣ለሩኩዕ ሲያጎነብስ አጎንብሱ፣ሱጁድ ሲወርድም ሱጁድ ውረዱ፡፡›› [በቡኻሪና በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    2 - በየትኛውም የሶላት ክንዋኔ ኢማሙን መቅደም ሐራም ነው፡፡ ነቢዩ ﷺ ለዚህ ክልከላ አጽንኦት ሲሰጡ አንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አንዳችሁ ከኢማሙ በፊት ራሱን ቀና ሲያደርግ፣ራሱን የአህያ ራስ እንዳያደርግ ወይም መልኩን ወደ አህያ መልክ እንዳይለውጠው አላህን አይፈራምን?›› [በቡኻሪና በሙስሊም የተዘገበ]

    3 - ረስቶ ከኢማሙ የቀደመ ሰጋጅ ወዲያውኑ ተመልሶ ኢማሙን የመከተል ግዴታ አለበት፡፡

    ሐደሥ ያለበትን (ጦሃራ የሌለውን) ሰው ተከትሎ መስገድ
    ሐደሥ ያለበት [ሐደሥ ያለበት ሰው ጦሃራ የሌለው ሰው ነው፡፡] መሆኑ ሶላቱ ካበቃ በኋላ ብቻ የታወቀ ካልሆነ በስተቀር፣ጦሃራ የሌለውን ሰው ተከትሎ መስገድ ትክክለኛ አይደለም፡፡ በዚህ ሁኔታ የመእሙሙ ሶላት ትክክለኛ ሲሆን ኢማሙ ግን ሶላቱን እንደገና መስገድ ይኖርበታል፡፡


Tags: