ሶላት አንድ ሙስሊም በመንፈሱና በአካሉ ወደ አላህ የሚመለስበት ታላቅ ዕባዳ ነው፡፡ በመሆኑም ራሱን በዚህ ብቻ በመጥመድ በተገቢው መንገድ ይፈጽመው ዘንድ፣ስነልቦናዊና አካላዊ መሰናዶና ዝግጅት ከሶላቱ መቅደም ተገቢ ይሆናል፡፡ ስለዚህም የሚከተለው ተደንግጎለታል፡፡
1 - እኽላስ (የልቦና ፍጹምነት)
‹‹አላህን፣ሃይማኖትን ለርሱ ብቻ አጥሪዎች ቀጥተኞች ኾነው ሊግገዙት፣ሶላትንም አስተካክለው ሊሰግዱ፣ዘካንም ሊሰጡ እንጅ ያልታዘዙ ሲኾኑ (ተለያዩ)፡፡ ይህም የቀጥተኛይቱ (ሃይማኖት) ድንጋጌ ነው፡፡›› [አል-በይናህ፡5]
አላህ ለርሱ ብቻ ተብሎ በፍጹምነት (በእኽላስ) የተሰራውንና ዝና ፈላጊነት፣ ልታይባይነትም ሆነ ምንም ዓይነት የሽርክ ዓይነት የሌለበትን ዕባዳ ብቻ ነው የሚቀበለው፡፡
2 - ዉዱእ ማሳመር (እስባግ)
ዉዱእ ማሳመር ማለት በተገቢውና በተሟላ ሁኔታ ዉዱእ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አላህ ኃጢቶችን የሚያብስበትንና ደረጃዎችን ከፍ የሚያደርግበትን ነገር ላመላክታችሁን? ሲሉ (ሰሓባ) ‹የአላህ መልእክተኛ ሆይ! አዎ ይንገሩን› አሉና ነቢዩ ﷺ ፡- (በብርድና በመሳሰለው) እየከበደ [ምቹ ያልሆነና ሰው የማይወደው አስቸጋሪ ሁኔታ፡፡] ዉዱእ አሟልቶ ማድረግ፣ወደ መስጊዶች እርምጃዎችን ማብዛት፣ከአንዱ ሶላት በኋላ ተከታዩን ሶላት መጠባበቅ ነው፡፡ ይህ ነው ለአላህ ትእዛዝ ተገዥ መሆን (ሪባጥ) ማለት፤ይህ ነው ነፍስን ለአላህ ማስገዛት (ሪባጥ) [ሪባጥ ራስን ለአላህ ትእዛዞች ማስገዛት ማለት ነው፡፡] ማለት፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ]
3 - በጊዜ አስቀድሞ ወደ ሶላት መሄድ
ተብኪር ሶላትን የመጠባበቅ ትሩፋት ለማግኘት ሲባል ቀደም ብሎ በመስጊድ መገኘት ማለት ነው፡፡ ከአቡ ሁረይራ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት የአላህ መልእክተኛ ﷺ፡- ‹‹አንዳችሁ ሶላትን በመጠበቅ ላይ እስካለ ድረስ ሶላት በመስገድ ላይ እንዳለ ይቆጠራል፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡
4 - የአላህ ውዳሴ - ዝክር
- ከቤት ሲወጡ እንዲህ ማለት ፡- ‹‹ብስምል’ላህ፣ተወከልቱ ዐለል’ሏህ፣ወላ ሐውለ ወላ ቁውወተ እል’ላ ብል’ላህ›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ]
ትርጉሙ ‹‹በአላህ ስም፣በአላህ ላይ ተማምኜ በርሱ እመካለሁ፤ኃይልም ሆነ ብልሃትና መላ ከአላህ ብቻ ነው፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ]
ማለት ነው፡፡ ‹‹አልሏሁም’መ አዑዙ ብከ አን አዲል’ለ አው ኡደል’ለ፣አው አዚል’ለ አው ኡዘል’ለ፣አው አዝሊመ አው ኡዝለመ፣አው አጅሀለ አው ዩጅሀሉ ዐለይ’የ፡፡›› ትርጉሙ ፡- ‹‹አላህ ሆይ! እንዳልጠም ወይም ሌሎች እዳያጠሙኝ፣እንዳልሳሳት ወይም ሌሎች እንዳያሳስቱኝ፣ሌሎችን እንዳልበድል ወይም ሌሎች እንዳይበድሉኝ፣እንዳልጃጃል ወይም ሌሎች እንዳያጃጅሉኝ ባንተ እጠበቃለሁ፡፡›› [በቡኻሪ ተዘገበ] ማለት ነው፡፡
- ወደ መስጊድ ሲሄድ አላህን በማውሳት እንዲህ ይላል፡- ‹‹አልሏሁም’መ እጅዐል ፊ ቀልቢ ኑረን፣ወፊ ልሳኒ ኑረን፣ወጅዐል ፊሰምዒ ኑረን፣ወጅዐል ፊበሰሪ ኑረን፣ወጅዐል ምን ኸልፊ ኑረን፣ወምን አማሚ ኑረን፣ወጅዐል ምን ፈውቂ ኑረን፣ወምን ተሕቲ ኑረን፣አልሏሁም’መ አዕጥኒ ኑራ፡፡›› ትርጉሙ ፡- ‹‹አላህ ሆይ! ልቤ ውስጥ ብርሃን፣በአንደበቴም ብርሃን አድርግልኝ፡፡ በመስሚያዬም ብርሃን አድርግልኝ፤በማያዬም ብርሃን አድርግለኝ፡፡ ከኋላዬም ብርሃን፣ከፊት ለፊቴም ብርሃን አድርግልኝ፡፡ ከበላዬም ብርሃን ከበታቼም ብርሃን አድርግልኝ፡፡ አላህ ሆይ! ብርሃን ስጠኝ፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ማለት ነው፡፡
5 - በጸጥታና በእርጋታ ወደ ሶላት መሄድ
ነቢዩ ﷺ፡- ‹‹እቃማ ስትሰሙ እርጋታና ጸጥታን ተላብሳችሁ ወደ ሶላት ሂዱ፤አትጣደፉ፤የደረሳችሁበትን ስገዱ፣ያመለጣችሁን አሟሉ፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡
6 - ወደ መስጊድ ሲገባ ዝክር ማድረግ
- መስጊድ ሲገባ የቀኝ እግርን በማስቀደም እንዲህ ማለት፡- ‹‹አዑዙ ብል’ላህ አልዐዚም፣ወብወጅህሂልከሪም፣ወሱልጣንህል ቀዲም፣ምነሽ’ሸይጣን አር’ረጂም፡፡›› ትርጉሙ ፡- ‹‹በኃያሉ አላህ፣ በተከበረው ፊቱና በመጀመሪያ የለሽ ሥልጣኑ ከተረገመው ሰይጣን እጠበቃለሁ፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ማለት ነው፡፡‹‹ብስምል’ላህ፣ወስ’ሰላቱ ወስ’ሰላሙ ዐላ ረሱሊል’ላህ፡፡››
‹‹አልሏሁም’መ እፍተሕ ሊ አብዋበ ረሕመትከ፡፡›› ትርጉሙ፡- ‹‹በአላህ ስም፣በአክብሮት የተቀናጀ እዝነትና ሰላም ለአላህ መልእክተኛ ይድረስ፡፡ [በሙስሊም የተዘገበ] አላህ ሆይ! የእዝነትህን በሮች ክፈትልኝ፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ማለት ነው፡፡
ከመስጊድ በሚወጣበት ጊዜ ግራ እግርን በማስቀደም እንዲህ ማለት፡- ‹‹ብስምል’ላህ፣ወስሰላቱ ወስሰላሙ ዐላ ረሱሊልላህ፡፡›› ‹‹አልሏሁምመ እንኒ አስአሉከ ምን ፈድሊከ፣አል’ሏሁም’መ አዕስምኒ ምነሽ’ሸይጣን አር’ረጂም፡፡›› ትርጉሙ፡- ‹‹በአላህ ስም፣በአክብሮት የተቀናጀ እዝነትና ሰላም ለአላህ መልእክተኛ ይድረስ፡፡ አላህ ሆይ! ከችሮታህ እለምንሃለሁ፤አላህ ሆይ! ከተረገመው ሸይጣን ጠብቀኝ፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ማለት ነው፡፡
7 - ሁለት ረክዓ ሳይሰግዱ አለመቀመጥ
ነቢዩ ﷺ፡- ‹‹አንዳችሁ ወደ መስጊደ ከገባ ሁለት ረክዓ ሳይሰግድ አይቀመጥ፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡
8 - ጣቶችን ከመቆላለፍ መቆጠብ
ነቢዩ ﷺ፡- ‹‹አንዳችሁ ዉዱእ አድርጎና ዉዱኡን አሳምሮ ወደ መስጊድ ለመሄድ ከወጣ ሶላት ውስጥ ነውና ጣቶቹን አይቆላልፍ፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡
9 - በአላህ ዝክር መጠመድ
ሶላትን በሚጠብቁበት የቆይታ ጊዜ፣ሌሎች ሰጋጆችን በድምጽ ካለመረበሽ ግዴታ ጋር በአላህ ዝክር፣በዱዓእና ቁርኣን በመቅራት መጠመድ ተገቢ ነው፡፡
10 - ኹሹዕ (ተመስጦ) በሶላት ውስጥ
ኹሹዕ የሶላት አስኳልና መንፈሱ ነው፡፡ ተመስጦና አስተውሎ የሌለበት ሶላት ሕይወት የሌለው በድን አካል ነው፡ እብን ረጀብ (ረዐ) እንዲህ ይላሉ፡- ‹‹ኹሹዕ በመሰረቱ የልብ ልስላሴ፣ገርነቱ፣እርጋታው፣ለአላህ ተገዥነቱ፣ተንበርካኪነቱና በኢማን ተቀጣጣይነቱ ነው፡፡ ልብ በተመስጦ ለአላህ ተገዥ ሲሆን እሱን የሚከተሉ በመሆናቸው የሰራ ገላና አከላት በሙሉ ተገዥ ይሆናሉ፡፡›› [እብን ረጀብ፣አልኹሹዕ መጽሐፍ] ኹሹዕ ስፍራው ልብ ውስጥ ሲሆን መገለጫው አካላዊ ተግባራት ናቸው፡፡
11 - በሶላቱ ውስጥ የነቢዩን ﷺ ሱንና አጥብቆ መከተል
ሶላት ነቢዩን ﷺ መከተል (እትባዕ) ግዴታ የሆነበት ዕባዳ በመሆኑ፣ሶላት ላይ ነቢዩ ﷺ ያላደረጉትን ነገር ከማድረግ ወይም እሳቸው ያላሉትን ነገር ከማለት መታቀብ ግዴታ ነው፡፡ ነቢዩ ﷺ ‹‹እኔ ስሰግድ እንዳያችሁኝ ስገዱ፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡