ሶላትን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች

5387

  1 - ተቀምጦ የሰገደ ሰው ሶላት

  ሀ- በነፍል ሶላት

  ግዴታ ያልሆነ ነፍል (ተጨማሪ) ሶላትን ተቀምጦ የሰገደ ሰው ሶላቱ ትክክለኛ ሲሆን፣ቆሞ የሰገደው ሰው ግማሽ ምንዳ ያገኝበታል፡፡ ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹ቆሞ ቢሰግድ በላጭ ነው፡፡ ተቀምጦ የሰገደ ሰው የቆመ ሰው አጅር ግማሽ አለው፡፡ ተኝቶ የሰገደ ሰው ተቀምጦ የሰገደ ሰው ግማሽ ምንዳ አለው፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ]

  ምክንያት (ዑዝር) ኖሮት ተቀመቀጦ የሰገደ ከሆነ ግን ሙሉ ምንዳ አለው፤ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹አንድ የአላህ አገልጋይ ቢታመም ወይም መንገደኛ ቢሆን እቤቱ እያለና በጤናማነቱ ይሰራው ከነበረ (ዕባዳ) እኩል ይጻፍለታል፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

  ለ- በግዴታ ሶላት

  ቆሞ መስገድ እስከተቻለ ድረስ ተቀምጦ የተሰገደ ሶላት ትክክለኛ አይሆንም፡፡

  2 - ንይ’ያ

  ንይ’ያን ከሚመለከቱ ብያኔዎች . . . .

  1 - ወደ ሶላት ሲገባ የተያዘውን የመስገድ ቁርጠኛ ውሳኔን (ንይያን) ሶላቱ ውስጥ ከገቡ በኋላ ማቋረጥ አይፈቀድም፡፡ በልቡ ሶላቱን ለማቋረጥ የወሰነ ሰው ሶላቱ ይቋረጥበታል፡፡ በመሆኑም እንደገና ከመጀመሪያው መጀመር ግዴታ ይሆንበታል፡፡

  2 - ለነፍል ሶላት ንይ’ያ አድርጎ ከጀመረ በኋላ ሶላቱን ወደ ግዴታ ሶላትነት መለወጥ አይፈቀድም፡፡

  3 - ለብቻው በነጠላ የግዴታ ሶላት ለመስገድ ንይ’ያ አድርጎ ከጀመረ በኋላ ጀማዓ የሚሰግዱ ሰዎች ከመጡ ንይ’ያውን ወደ ነፍልነት ለውጦ በሁለት ረክዓ መፈጸም ይፈቀድለታል፡፡ ከዚያ ሶላቱን በሰላምታ አብቅቶ ከጀማዓው ጋር ይሰግዳል፡፡

  3 - ፋቲሓን መቅራት

  አንድ ሰጋጅ ድምጽ ከፍ ተደርጎ በሚቀራበት ሶላት በጀማዓ መእሙም ሆኖ እየሰገደ ቢሆን እንኳ ፋቲሓን ለራሱ መቅራት ግዴታ ነው፡፡ ዑብባዳ ብን አስሳምት (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት፡- ‹‹የፈጅርን ሶላት የአላህ መልእክተኛን ﷺ ተከትለን ስንሰግድ የአላህ መልእክተኛ ﷺ ቅራኣው (በመእሙሞቹ ቅራኣ ምክንያት) ከበደባቸው፤ሶላቱን ካበቁ በኋላ ከኢማማችሁ ጀርባ ሆናችሁ (ቁርኣን) ትቀራላችሁ መሰል? ሲሉ የአላህ መልእክተኛ ሆይ! አዎ አልናቸው፡፡ እሳቸውም ﷺ የመጽሐፉን የመክፈቻ ምዕራፍ (ፋቲሓን) ብቻ እንጂ አታድርጉ፣(ፋቲሓን) ያልቀራበት ሰው ሶላት የለውምና፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] አሉ ብለዋል፡

  4 - ኣሚን ማለት

  ተእሚን ማለትም ኣሚን ማለት ለአንድ ሰጋጅ፣ኢማምም ይሁን መእሙም፣ወይም ለብቻው የሚሰግድ፣በግዴታም ይሁን በነፍል ሶላት፣ድምጽ ከፍ በሚልበትም ሆነ በማይልበት ግዴታ ነው፡፡

  ከፍ በሚልበት ከፍ አድርጎ ከፍ በማይልበት ድምጽ ሳያሰማ ኣሚን ይላል፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹ኢማሙ ኣሚን ሲል ኣሚን በሉ፣ተእሚኑ ከመላእካ ተእሚን (ኣሚን ማለት) ጋር የተገጣጠመለት ሰው ያለፈው ኃጢአቱ ይሰረይለታልና፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

  5 - ኢማሙ ዝም የሚልባቸው ቦታዎች

  1 - በመክፈቻው ተክቢራና በፋቲሓ መካከል የመክፈቻውን ዱዓእ ለመቅራት፡፡

  2 - በፋቲሓ ቅራኣና በሱራ መካከል ኢማሙ ዝም ስለማለቱ በሱንና የተረጋገጠ ነገር የለም፡፡

  3 - ቅራኣ ካበቃ በኋላ ከሩኩዕ በፊት ያለው ዝምታ፡

  6 - ያመለጠ የግዴታ ሶላት (ቀዷእ) ሲሰገድና በሱንና ሶላት ድምጽን ከፍ ማድረገ

  አንድ ሰው ሶላት ቢያመልጠውና ሰግዶ መክፈል ቢፈልግ ድምጹን ከፍ አድርጎ ይቀራል ወይስ ሳያድርግ? ግምት ውስጥ የሚገባው ሶላቱ እንጂ ተሰግዶ የሚከፈልበት ጊዜው አይደለም፡ ድምጽ ከፍ የሚደረግበትን ሶላት በቀን ሰግዶ የሚከፍል ቢሆን ድምጹን ከፍ አድርጎ ይቀራል፡፡ በነፍል ሶላቶች ላይ ከፍ ስለመደረጉ ማስረጃ ካላቸው እንደ ተራዊሕና ኹሱፍ ካሉት በስተቀር፣በሌሎቹ ሱንናው ከፍ ሳያደርጉ መቅራት ነው፡፡

  7 - እጆችን ከፍ ማድረግ

  በሚከተሉት ቦታዎች ላይ እጆች ከፍ ይደረጋሉ ፡-

  1 - በእሕራም ተክቢራ ጊዜ፡፡

  2 - በሩኩዕ ተክቢራ ጊዜ፡፡

  3 - ከሩኩዕ ቀና ሲሉ፡፡

  4 - ከመጀመሪያው ተሸሁድ ተነስቶ ሲቆሙ

  8 - ያመለጠ ረክዓን ማሟላት

  አንድ ሰጋጅ ከኢማሙ ጋር ደርሶ አብሮት ሩኩዕ ካደረገ ለረክዓው ደርሷል፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹ለሩኩዕ የደረሰ ሰው ረክዓውን ደርሶበታል፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

  9 - እርጋታ (ጡመእኒና)

  እርጋታ (ጡመእኒና) በሁሉም የሶላት ክፍሎች ውስጥ ሶላቱ ያለርሱ ትክክለኛ የማይሆን አንዱ የሶላት ማእዘን ነው፡፡ አቡ ሁረይራ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት፡- የአላህ መልእክተኛ ﷺ ወደ መስጊድ ሲገቡ አንድ ሰውየ ገብቶ ሶላት ሰገደና መጥቶ ለአላህ መልእክተኛ ﷺ ሰላምታ አቀረበ፡፡ የአላህ መልእክተኛ ﷺ ሰላምታውን መለሱና ፡- ‹‹አልሰገድክምና ተመልሰህ ስገድ›› አሉት፡፡ ሰውየው ተመለሰና አስቀድሞ ሰግዶት በነበረው ሁኔታ ሰግዶ ወደ አላህ መልእክተኛ ﷺ ተመልሶ በመምጣት ሰላምታ አቀረበላቸው፡፡ ‹‹በአንተ ላይም ሰላም ይሁን›› አሉትና ፡- ‹‹አልሰገድክምና ተመልሰህ ስገድ›› አሉት፡፡ ሦስት ጊዜ ያንኑ ሲደጋግሙበት ሰውየው ‹እርስዎን በእውነት በላክዎት አላህ እምላለሁ ከዚህ በላይ አላውቅምና አስተምሩኝ› አላቸው፡፡ እሳቸውም ፡- ‹ለሶላት ስትቆም አል’ሏሁ አክበር›› በል፤ከዚያም የምታውቀውን ያህል ቁርኣን ቅራ፤ከዚያም ለሩኩዕ ከወገብህ ጎንበስ በልና ሩኩዕ ላይ እርጋ፤ከዚያም ቀጥ ብለህ እስክትቆም ድረስ ቀና በል፤ከዚያም ሱጁድ ወርደህ በሱጁዱ ላይ እርጋ፤ከዚያም ተረጋግተህ እስክትቀመጥ ድረስ ቀና በል፤በሶላትህ በሙሉ ይህንኑ አድርግ፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] አሉት ብለዋል፡፡

  10 - ምላስን ማላወስ

  ቁርኣን ሲቀራ፣ተክቢራና ዝክሮች ሲደረጉ በልብ ብቻ መቅራት በቂ አይደለም፡፡ በአንደበትም መናገር የግድ ነው፡፡ አነስተኛው ሲቀራ ምላስና ከንፈሮችን ማላወስ ነው፡፡

  11 - የሱጁድ አወራረድ

  ሱጁድ የሚወረደው በሰባት አካላት ነው፡፡ ነቢዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፡- ‹‹አንድ የአላህ አገልጋይ ሱጁድ ሲያደርግ ከርሱ ጋር ሰባት አካላት ሱጁድ ይወርዳሉ ፡- ፊቱ፣ሁለት መዳፎቹ፣ሁለት ጉልበቶቹና ሁለት አግሮቹ፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ]

  12 - አመልካች ጣትን መቀሰር

  ሱንናው በተሸሁድ ጊዜ አመልካች ጣትን መቀሰር ነው፡፡ ዋእል ብን ሑጅር (ረዐ) ባስተላለፉት ሐዲስ ‹‹ከዚያም ጣታቸውን ቀና አደረጉና ሲያንቀሳቅሱትና ዱዓእ ሲያደርጉበት አየሁ፡፡›› [በነሳኢ የተዘገበ] የሚል ተመልክቷል፡፡

  ተገቢ አይደለም

  - ንይ’ያን በአንደበት መናገርና ከእሕራም ተክቢራ ጋር ማቆራኘት ግዴታ ነው ማለት፡፡

  - ‹‹ረብ’በና ወለከል ሐምዱ›› ሲሉ ‹‹ወሽ’ሹክር›› የሚል ቃል መጨመር፡፡ ይህ ጭማሪ ከአላህ መልእክተኛﷺ መተላለፉ አልተረጋገጠም፡፡

  - ‹‹ሰይ’ድና›› የሚል ተጨማሪ ቃል በተሸሁድ ወይም ሶላት ውስጥ በነቢዩ ﷺላይ ሰላት ስናወርድ መጨመር፡፡

  - በሰላምታ ጊዜ በቀኝ እጅ ወደ ቀኝ፣በግራው ወደ ግራ ማመልከት፡፡

  - የሰጋጆች ከሰላምታ በኋላ እርስ በርስ መጨባበጥ፣አንዱ ‹‹ሐረመን›› ሲል ሌላው ‹‹ጀምዐን›› ማለትና የመሳሰለው፡፡

  - አንዳንዶች የሚያደርጉትና አንዱ ኣየት አልኩርሲ ቀርቶ ሱብሓነል’ሏህ ሲል ሌሎች ሱብሓነል’ሏህ . . . ማለትን የመሳሰለ ሁሉ፡፡

  - ከዱዓእና ከዝክር በኋላ ፊትን ማበስ፡፡