የሶላት አሰጋገድ

11705

    ፡- ‹‹እኔ ስሰግድ እንዳያችሁኝ ስገዱ፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡

    ዓእሻ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ፡- ‹‹የአላህ መልእክተኛ ﷺ ሶላትን በተክቢር (አሏሁ አክበር) እና በ‹‹አልሐምዱ ሊል’ላህ ረብ’ቢል ዓለሚን›› ይከፍቱ ነበር፡፡ ለሩኩዕ ሲያጎነብሱ ራሳቸውን ወደ ላይ ቀና አያደርጉም፣በጣምም ዝቅ አያደርጉም፤በሁለቱ መካከል (ከጀርባቸው ጋር የተስተካከለ) ያደርጉ ነበር እንጂ፡፡ ራሳቸውን ከሩኩዕ ቀና ሲያደርጉ ቀጥ ብለው እስኪቆሙ ድረስ ሱጁድ አይወርዱም ነበር፡ ራሳቸውን ከሱጁዱ ቀና ሲያደርጉም ቀጥ ብለው እስኪቀመጡ ድረስ ለ(ሁለተኛው) ሱጁድ አይወርዱም ነበር፡፡ በየሁለቱ ረክዓም አት’ተሕይያቱ ይሉ ነበር፡፡ በግራ እግራቸው ላይ ሲቀመጡ የቀኝ እግራቸውን (ጣቶችን መሬት ላይ በማሳረፍ) ያቆሙ ነበር፡፡ የሰይጣን ዓይነት ቁጥጥ ማለትን ይከለክሉ ነበር፡፡ አንድ ሰው እንደ አውሬ ሁለት ክንዶቹ ላይ እንዳይሞረኮዝም ይከለክሉ ነበር፡፡ ሶላትን በተስሊም (ሰላምታ) ይጨርሱ ነበር፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    ፊትን ወደ ቅብላ ማዞርና የመክፈቻ እሕራም

    - መስገድ የፈለገ ሰው ፊቱን ወደ ቅብላ አዙሮ በአላህ ﷺ ፊት መቆሙ እየተሰማው በሶላቱ የተመሰጠ ሆኖ ይቆማል፡፡

    - ከዚያም በልቡ ለመስገድ ቁርጠኛ ሃሳብ ያደርጋል፡፡ ንይያ በልብ ሲሆን በአንደበት መናገር አይፈቀድም፡፡ የልብን ንይ’ያ በቃል መናገር ብድዓ ነው፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹ሥራዎች (የሚለኩት ከጀርባቸው ባለው ቁርጠኛ) ውሳኔ ነው፤እያንዳንዱ ሰውም በንይ’ያው መሰረት ነው የሚያገኘው፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    - ከዚያ ሁለት እጆቹን በትከሻዎች ወይም ጆሮዎች ትይዩ ከፍ አድርጎ ‹‹አል’ሏሁ አክበር›› [በሙስሊም የተዘገበ] ይላል፡፡

    - ከዚያም ከደረቱ በታች ቀኝ እጁን በግራው [በአሕመድ ተዘገበ] ላይ አድርጎ የግራ እጁን በቀኙ ይይዛል፡፡

    የመክፈቻው ዱዓእና የፋቲሓ ንባብ (ቅራኣ)

    - ሰጋጁ ራሱን ትንሽ ዝቅ አድርጎ እይታውን ሱጁድ መውረጃ ቦታው [በቡኻሪ የተዘገበ] ላይ ያደርጋል፤ከዚያም ፡- ‹‹ሱብሓነከ አል’ሏሁም’መ ወብሐምድከ፣ተባረከ እስሙከ፣ወተዓላ ጀድ’ዱከ፣ወላ እላሀ ገይሩከ፡፡›› ይላል፡፡ ትርጉሙ ፡- ‹‹አላህ ሆይ! ጥራት ይገባህ፤ምስጋናም ላንተ ይሁን፤ስምህ የተቀደሰ ነው፤ግርማና ኃያልነትህ ላቀ፤ካንተ በስተቀርም ሌላ አምላክ የለም፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ማለት ነው፡፡

    - በመቀጠልም ድምጽ ሳያሰማ ፡- ‹‹አዑዙ ብል’ላሂ ምነሽ’ሸይጣን አር’ረጂም›› ‹‹ብስምል’ላህር’ረሕማንር’ረሒም›› ይላል፡፡ ትርጉሙ ፡- ‹‹ከተረገመው ሰይጣን በአላህ እጠበቃለሁ፡፡›› ‹‹በአላህ ስም፣እጅግ በጣም ርኅሩኅ በጣም አዛኝ በኾነው፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ማለት ነው፡፡

    - ከዚያ በኋላ ፋቲሓን ይቀራና [በቡኻሪ የተዘገበ] ‹‹ኣሚን›› ይላል፡፡ ኣሚን ማለት ‹‹አላህ ሆይ! ተቀበል›› ማለት ነው፡፡

    - ከዚያም ሰጋጁ ከፋቲሓ በኋላ አንድ የቁርኣን ምዕራፍ ወይም ከቁርኣን የተመቸውን ያህል በመጀመሪያዎቹ ሁለት ረክዓዎች ይቀራል፡ በሱብሕ፣በመጀመሪያዎቹ ሁለት የመግሪብና የዕሻእ ረክዓዎች ድምጽ ከፍ ተደርጎ ይቀራል፡፡

    ሩኩዕና ከሩኩዕ ቀና ማለት

    ሰጋጁ እጆቹን ከፍ አድርጎ ‹‹አል’ሏሁ አክበር›› በማለት ለሩኩዕ ከወገቡ ጎንበስ ይላል፡ ጣቶች የተዘረዘሩ ሆነው በመዳፎቹ ጉልበቶቹን ይይዛል፡፡ ራሱና ጀርባው እኩል ይሆናሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ሦስቴ ‹‹ሱብሓነ ረብ’ቢየል ዐዚም›› ይላል፡፡ ይህም ‹‹ለኃያሉ ጌታዬ ጥራት ይገባው›› [በትርምዚ የተዘገበ] ማለት ነው፡፡

    ከዚያም ከሩኩዕ ራሱን ቀና በማድረግ (ኢማሙና ለብቻው የሚሰግድም) ፡- ‹‹ሰምዐል’ሏሁ ልመንሐሚደህ›› ይላል፡፡ ሁሉም አንድ ላይ ‹‹ረብ’በና ወለከል ሐምዱ፣ምልአስ’ሰማዋት ወምልአልአርድ፣ወምልአ ማበይነሁማ፣ወምልአ ማሽእተ ምን ሸይእን በዕደህ›› ይላሉ፡፡ ትርጉሙ፡- ‹‹አላህ የአመስጋኝን ምስጋና ሰሚ አመስጋኝ ነው፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ]

    ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው፡- ‹‹ጌታችን ሆይ! ምስጋና ላንተ ይሁን፤ሰማያትን የሞላ፣ምድርን ያጥለቀለቀና በሁለቱ መካከል ያለውን ሁሉ የሞላ፣ያሻህን ሁሉ ሙሉ ምስጋና ይድረስህ፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ] ማለት ነው፡፡ ከሩኩዕ ቀና ሲል እጆቹን ከሩኩዕ በፊት እንዳደረገው ሁሉ ደረቱ ላይ መያዝ የተወደደ ነው፡፡

    ሱጁድና ከሱጁድ ቀና ማለት

    - ሰጋጁ ‹‹አል’ሏሁ አክበር›› ብሎ ሱጁድ ይወርዳል፡፡ መጀመሪያ መሬት የሚደርሱት ጉልበቶቹ ሲሆኑ ከዚያ ሁለት እጆቹ [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] በመቀጠልም ግንባሩና አፍንጫው ናቸው፡፡

    መዳፎቹን በጆሮዎቹ ወይም በትከሻዎቹ ትይዩ መሬት ላይ ይዘረጋል፤ጣቶች ወደ ቅብላ አቅጣጫ ይሆናሉ፤ክንዶቹን ከመሬት ከፍ አድርጎ ከክንድ እስከ ትከሻ ያለውን ከጎኖቹ [በቡኻሪ የተዘገበ] ፣ሆዱን ከጭኖቹ ያራርቃል፡፡

    ሦስት ጊዜ ፡- ‹‹ሱብሓነ ረብ’ቢየል አዕላ›› ይላል፡፡ ትርጉሙ ‹‹ከሁሉ በላይ የላቀው ጌታዬ ጥራት ይገባው›› ማለት ነው፡፡ በሱጁድ ውስጥ ዱዓእ ያበዛል፡፡ [በሙስሊም የተዘገበ]

    - ከዚያም ‹‹አል’ሏሁ አክበር›› እያለ ራሱን ቀና ያደርጋል፡፡ እጆቹን ከፍ አያደርግም፡፡ ግራው ላይ በመቀመጥ [በትርምዚ የተዘገበ] ጣቶቹን ወደ ቅብላ አድርጎ ቀኙን ተረከዝ ያቆማል፡፡ ሁለት እጆቹን ጣቶችን ወደ ቅብላ በማድረግ ጭኖቹ ላይ ይዘረጋቸውና፡- ‹‹አል’ሏሁምመ እግፍርሊ፣ወርሐምኒ፣ወጅቡርኒ፣ወህድኒ፣ወርዙቅኒ›› ይላል፡፡

    ትርጉሙ ፡- ‹‹አላህ ሆይ! ኃጢአቴን ማረኝ፤እዘንልኝም፤ድክመቴንም ጠግነኝ፤ምራኝም፤ሲሳይም ለግሰኝ፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ማለት ነው፡፡

    - ከዚያም ‹‹አል’ሏሁ አክበር›› ብሎ በመጀመሪያው ዓይነት ሁለተኛውን ሱጁድ ያደርጋል፡፡

    - ከዚያም ‹‹አል’ሏሁ አክበር›› እያለ ቀና ብሎ ለአፍታ ይቀመጣል፤ይህም የእስትራሓ (የማረፊያ) መቀመጥ ተብሎ ይጠራል፡፡ ማሊክ ብን አል ሑወይሪሥ (ረዐ) የነቢዩን ﷺ አሰጋገድ በገለጹበት ሐዲስ ውስጥ ‹‹ቀጥ ብለው ሳይቀመጡ ተነስተው አልቆሙም፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    - በመቀጠል ‹‹አል’ሏሁ አክበር›› እያለ እጆቹ ላይ ተሞርክዞ ለሁለተኛው ረክዓ ተነስቶ ይቆማል፡፡ [በቡኻሪ የተዘገበ]

    - ከዚያም የመክፈቻው ዱዓእ ብቻ ሲቀር ሁለተኛውን ረክዓ በመጀመሪያው ዓይነት ይሰግዳል፡፡

    ተሸሁድ

    ሰጋጁ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ረክዓዎች ሲያበቃ ለመጀመሪያው ተሸሁድ በታጠፈ ግራ እግሩ ላይ ተቀምጦ ቀኙን ያቆማል፡፡ ሁለት እጆቹን ጭኖቹ ላይ አድርጎ የግራውን ይዘረጋል፡፡ የቀኝ እጁን ትንሹንና የቀለበት ጣቶቹን ጨብጦ ረዥሙን ከአውራ ጣት ጋር በማክበብ አመልካች ጣቱን ይዘረጋና በተሸሁድ ጊዜ ቀና አድርጎ ይቀስረዋል፡፡

    እይታውን አመልካች ጣቱ ላይ አሳርፎ ፡- ‹‹አት’ተሕይ’ያቱ ሊል’ላህ፣ወስ’ሰለዋቱ ወጥ’ጠይባቱ፤አስ’ሰላሙ ዓለይከ አይ’ዩሀን’ነቢዩ ወረሕመቱል’ሏሂ ወበረካቱሁ፣ አስ’ሰላሙ ዐለይና ወዐላ ዕባድል’ላህ አስ’ሷሊሒን፤አሽሀዱ አን ላእላሀ እል’ላል’ሏህ ወአሽሀዱ አን’ነ ሙሐመደን ዐብዱሁ ወረሱሉህ፡፡›› ይላል፡፡

    ትርጉሙ ፡- ‹‹ክብር፣ሶላቶችና መልካም ነገሮች ሁሉ የአላህ ናቸው፡፡ አንቱ ነቢዩ ሆይ! የአላህ ሰላም፣እዝነቱና በረከቶቹ ለርስዎ ይሁን፡፡ ሰላም ለኛና ለደጋጎቹ የአላህ አገልጋዮች ይሁን፡፡ ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ አለመኖሩን እመሰክራለሁ፡፡ ሙሐመድም የአላህ አገልጋይና መልእክተኛው መሆናቸውን እመሰክራለሁ፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ማለት ነው፡፡

    በመቀጠል ሶላቱ ከሁለት ረክዓ የሚበልጥ ከሆነ እጆቹን ከፍ አድርጎ ‹‹አል’ሏሁ አክበር›› እያለ ተነስቶ ይቆማል፡፡ በቀሪዎቹ ረክዓዎች ከፋቲሓ በስተቀር ሌላ አይቀራም፡፡

    - በመጨረሻው ተሸሁድ መቀመጫውን ከመሬት አድርሶ በመቀመጥ የግራ እግሩን በቀኝ በኩል አውጥቶ መሬት ላይ ያስተኛል፤የቀኝ እግሩ ተረከዝ ይቆማል፡፡ [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ]

    በመጀመሪያው ተሸሁድ በቀረበው ላይ የሚከተለውን ጨምሮ ይላል፡- ‹‹አልሏሁም’መ ሶል’ል ዐላ መሐመድን ወዐላ ኣል ሙሐመድን ከማ ሶል’ለይተ ዐላ ኢብራሂመ ወዐላ ኣል ኢብራሂመ እን’ነከ ሐሚዱን መጂድ፡፡ አልሏሁም’መ ባሪክ ዐላ ሙሐመድ ወዐላ ኣል ሙሐመድን ከማባረክተ ዐላ ኢብራሂመ ወዐላ ኣል ኢብራሂመ እን’ነከ ሐሚዱን መጂድ፡፡››

    ትርጉሙ ፡- ‹‹አላህ ሆይ! ከአክብሮት የተቀናጀ እዝነትህን ለኢብራሂምና ለቤተሰቦቻቸው እንዳወረድክላቸው ሁሉ ለሙሐመድና ለቤተሰቦቻቸው አውርድላቸው፡፡ ኢብራሂምና ቤተሰቦቻቸውን ብሩክ እንዳደረግሃቸው ሁሉ ሙሐመድንና ቤተሰቦቻቸውን ብሩክ አድርጋቸው፡፡ አንተ በዓለማት ሁሉ ምስጉኑና ኃያሉ ነህና፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ማለት ነው፡፡

    - ከዚያም ፡- ‹‹አልሏሁም’መ እን’ኒ አዑዙ ብከ ምን ዐዛብ ጀሀነም፣ወምን ዐዛብል ቀብር፣ወምን ፍትነትል መሕያ ወልመማት፣ወምን ሸር’ር ፍትነትል መሲሕ አድ’ደጅ’ጃል›› ይላል፡፡ ትርጉሙ፡- ‹‹አላህ ሆይ! ከጀሀነም ስቃይ፣ከመቃብር ውስጥ ስቃይም፣ከመኖርና ከመሞት ፈተናም፣ከሐሳዊው መሲሕ (ከደጃል) ፈተናም በአንተ እጠበቃለሁ፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ማለት ነው፡፡

    ተስሊም (ሰላምታ)

    በሶላቱ መጨረሻ ላይ ሰጋጁ አንገቱን ወደ ቀኝና ወደ ግራ እያዞረ ፡- ‹‹አስ’ሰላሙ ዓለይኩም ወረሕመቱል’ሏህ›› በማለት ሶላቱን በሰላምታ ያጠናቅቃል፡፡ ትርጉሙ ‹‹የአላህ ሰላምና እዝነቱ በናንተ ላይ ይሁን፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ማለት ነው፡፡

    የእሕራም ተክቢራ
    የፋቲሓ ቅራኣ
    ሩኩዕና ከሩኩዕ ቀና ማለት
    ሱጁድና ከሱጁድ ቀና ማለት
    በሁለቱ ሱጁዶች መካከል መቀመጥ
    ለመጨረሻው ተሸሁድ መቀመጥ
    ተስሊም

    ከድህረ ሶላት ዝክሮች በከፊል

    - ሦስት ጊዜ ‹‹አስተግፍሩል’ሏህ›› (አላህ ሆይ! ምሕረት እለምናለሁ) ማለት፡፡ ‹‹አልሏሁም’መ አንተስ’ሰላም፣ወምንከ አስ’ሰላም፣ተባረክተ ያዘልጀላል ወል እክራም›› ማለት፡፡ ትርጉሙ፡- ‹‹አላህ ሆይ! አንተ የሰላም ባለቤት ነህ፣የሰላም ምንጭም አንተው ነህ፤የግርማ ሞገስና የከበሬታ ባለቤት ሆይ! አንተ ቅዱስ ነህ፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ማለት ነው፡፡

    - ‹‹ላ እላሀ እል’ላል’ሏህ ወሕደሁ ላሸሪከ ለሁ፣ለሁልሙልኩ ወለሁልሐምዱ ወሁወ ዐላ ኩል’ል ሸይእን ቀዲር፤አልሏሁም’መ ላማኒዐ ልማ አዕጠይተ፣ወላ ሙዐጢየ ልማ መነዕተ፣ወላ የንፈዑ ዘልጀድ’ድ ምንከል ጀድ’ድ››

    ትርጉሙ፡- ‹‹ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም፡፡ እርሱ አንድ ነው፤ተጋሪ (ሸሪክ) የለውም፡፡ ንግሥና የርሱ ብቻ ነው፡፡ ምሥጋናም የርሱ ነው፡፡ እርሱ በሁሉም ነገር ላይ ቻይ ነው፡፡ አላህ ሆይ! አንተ የሰጠኸውን የሚከለክል የለም፤አንተ የከለከልከውንም የሚሰጥ የለም፤ትልቅነትና ዝና ካንተ (ቅንጣት) አያድንም፣አንተ ዘንድ አይጠቅምም፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ማለት ነው፡፡

    - ‹‹ላ እላሀ እል’ላል’ሏህ ወሕደሁ ላሸሪከ ለሁ፣ለሁልሙልኩ ወለሁልሐምዱ ወሁወ ዐላ ኩል’ል ሸይእን ቀዲር፤ላሐውለ ወላቁው’ወተ እል’ላ ብል’ላህ፤ላእላሀ እል’ላል’ሏህ፣ወላ ነዕቡዱ እል’ላ እይ’ያሁ፣ለሁን’ንዕመቱ ወለሁል ፈድሉ፣ወለሁ አሥ’ሠናኡል ሐሰን፣‹‹ላእላሀ እል’ላል’ሏሁ ሙኽሊሲነ ለሁድዲነ ወለው ከሪሀል ካፍሩን›› ማለት፡፡

    ትርጉሙ ፡- ‹‹እርሱን ብቻ እንጂ ሌላ አናመልክም፣ጸጋዎች ሁሉ የርሱ ናቸው፤ችሮታና መልካም ውዳሴም የርሱ ናቸው፡፡ ከአላህ በስተቀር ሌላ አምላክ የለም፣ከሃዲዎች ቢጠሉትም ሃይማኖትን ለርሱ ብቻ ፍጹም እናደርጋለን፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ማለት ነው፡፡

    - ሰላሳ ሦስት ጊዜ ‹‹ሱብሓነል’ሏህ ወልሐምዱሊ’ላህ ወል’ሏሁ አክበር›› ማለት፡፡ ትርጉሙ ፡- ‹‹ጥራት ለአላህ የተገባ ነው፣ምስጋናም ለአለህ ይድረስ፣አላህ ከሁሉም በላይ ኃያል ነው፡፡›› ማለት ነው፡፡ ‹‹ላእላሀ እል’ላል’ሏህ ወሕደሁ ላሸሪከ ለሁ ፣ለሁልሙልኩ ወለሁልሐምዱ ወሁወ ዐላ ኩል’ል ሸይእን ቀዲር›› [በሙስሊም የተዘገበ]

    - ‹‹አልሏሁም’መ አዒን’ኒ ዐላ ዝክሪከ ወሹክሪከ ወሑስን ዕባደትከ›› ትርጉሙ ፡- ‹‹አላህ ሆይ! ባንተ ውዳሴ፣ባንተ ምስጋና እና በሰመረ አምልኮትህ ላይ አግዘኝ፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ማለት ነው፡፡

    - ኣየት አልኩርሲ (አልበቀራ፡255)፣ሱረት አልእኽላስ፣አልፈለቅና አንናስን [በነሳኢ የተዘገበ] መቅራት፡፡ ከሱብሕ ሶላት ሰላምታ በኋላ ፡- ‹‹አልሏሁምመ - እን’ኒ አስአሉከ ዕልመን ናፊዐን፣ወሪዝቀን ጠይ’ይበን፣ወዐመለን ሙተቀበላ›› ማለት፡፡

    ትርጉሙ ፡- ‹‹አላህ ሆይ! ጠቃሚ እውቀት፣ጥሩ ሲሳይና ተቀባይነት ያለው ሥራ እለምንሃለሁ፡፡››[በእብን ማጀህ የተዘገበ]ማለት ነው፡፡

    ጠቃሚ ነጥብ
    የሴት አሰጋገድ ልክ እንደ ወንዱ አሰጋገድ ነው፡፡