የሐጅ ማእዘናት ዋጅቦችና ሱናዎች

3458

    የሐጅ ማእዘናት

    1 - እሕራም፡፡

    ነቢዩ ﷺ ‹‹ሥራዎች (የሚለኩት ከጀርባቸው ባለው ቁርጠኛ) ውሳኔ ነው፤እያንዳንዱ ሰውም በንይ’ያው መሰረት ነው የሚያገኘው፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    2 - በሶፋና መርዋ መካከል መመላለስ (ሰዕይ)፡፡

    ነቢዩ ﷺ ‹‹ተመላለሱ፤አላህ መመላለስን (ሰዕይን) ግዴታ አድርጎባችኋልና፡፡›› [በአሕመድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    3 - በምድረ ዐረፋ መቆም (መገኘት)፡፡

    ነቢዩ ﷺ ‹‹ሐጅ ዐረፋ ነው፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    4 - ጠዋፉል እፋዷ ማድረግ፡፡

    አላህ ፡- ‹‹በጥንታዊውም ቤት ይዙሩ፡፡›› [አል-ሐጅ:29] ብሏልና፡፡

    - ማሳሰቢያ...

    ከሐጅ ማእዘናት ውስጥ አንዱን ማእዘን የተወ ሰው፣ የተተወው እሕራም ከሆነ ኒይያ አላደረገምና ዕባደው አልታሰረም፡፡ ያለ ኒይያም ዕባዳ የለም፡፡ ከእሕራም ውጭ ሌላ ሩክን ከሆነ ሩክኑን እስኪያሟላ ዕባዳው ሊፈጸም አይችልም፡፡

    የሐጅ ዋጅቦች

    1 - ከሚቃት እሕራም ማድረግ፡፡

    ነቢዩ ﷺ ሚቃቶችን ከጠቀሱ በኋላ ‹‹እነዚህ ለነሱና የነዚያ ነዋሪዎች ሳይሆኑ በነሱ በኩል ሐጅና ዑምራ ፈልገው ለሚመጡትም ናቸው፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ]

    ብለዋል፡፡

    2 - ቀን በዐረፋ የተገኘ (የቆመ) ሰው ነቢዩ ﷺ እስከ ጸሐይ መጥለቅ ድረስ የቆሙ በመሆኑ እስከ ጸሐይ መጥለቅ ድረስ መቆም፡፡

    3 - በሙዝደሊፋ ማደር፡፡

    ነቢዩ ﷺ ሙዝደሊፋ አድረው ‹‹ኡመቴ (ሕዝቦቼ) የዕባዳ አፈጻጸማቸውን ከኔ ይውሰዱ፣ካሁኑ ዓመቴ በኋላ ዳግም ከነሱ መገናኘት አለመገናኘቴን አላውቅምና፡፡› [በእብን ማጃህ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

    በተጨማሪም ነቢዩ ﷺ ለአቅመ ደካማ ሙስሊሞች ያለማደር ፈቃድ የሰጡ በመሆኑ ይህም ማደር አስፈላጊ መሆኑን የሚያመለክት ሲሆን፣አላህ መሽዐሩል ሐራም ዘንድ እርሱን እንዲያወሱ አዟል፡

    4 - የአይ’ያም አትተሸሪቅ ቀናት ሌሊቶችን አዳር በሚና ማድረግ፡፡

    ነቢዩ ﷺ ለእረኞች ከሚና ውጭ እንዲያድሩ ፈቃድ የሰጡ መሆናቸው [በአቡ የዕላ ሙስነዳቸው ውስጥ የተዘገበ] የተረጋገጠ ሲሆን ይህም ሚና ውስጥ ማደር በመሰረቱ ግዴታ መሆኑን ያመለክታል፡፡

    5 - ጠጠሮችን መወርወር፡፡

    አላህ እንዲህ ብሏል፡ ‹‹በተቆጠሩ ቀኖችም ውስጥ (በሚና ጠጠሮችን ስትወረውሩ) አላህን አውሱ፡፡›› [አል-በቀራህ:203] የተቆጠሩ ቀናት ማለት ሦስቱ የተሸሪቅ ቀናት ናቸው፡፡

    ጠጠሮችን መወርወር የአላህ ዝክርና ውዳሴ አካል ነው፡፡ ነቢዩ ﷺ ፡- ‹‹በቤቱ (በከዕባ) ዙሪያና በሶፋና መርዋ መካከል ጦዋፍ የተደረገው፣የጠጠረሮች ውርወራም የአላህን ዝክር ቋሚ ለማድረግ ነው፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

    6 - ጸጉር መላጨት ወይም ማሳጠር፡፡

    አላህ ፡- ‹‹አላህ የሻ እንደ ኾነ ጸጥተኞች ኾናችሁ፣ራሶቻችሁን ላጭታችሁ፣አሳጥራችሁም የማትፈሩ ስትኾኑ፣የተከበረውን መስጊድ በእርግጥ ትገባላችሁ፤›› [አል-ፈትሕ:27] ብሏል፡፡

    7 - የመሰናበቻ ጠዋፍ፡፡

    ከእብን ዐባስ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ‹‹ሰዎች (ሐጃጆች) የመጨረሻ ተግባራቸውን ቤቱን መዞር (ጠዋፍ) እንዲያደርጉ የታዘዙ ሲሆን የወር አበባ ካለባቸው ላይ ትእዛዙ ተቃሏል፡፡›› [በሙስሊም ተዘገበ] ብለዋል፡፡

    የሐጅ ሱናዎች

    1 - ለእሕራም ገላን መታጠብና ሽቶ መቀባት፡፡

    2 - ነጭ ሽርጥና ፎጣ መልበስ፡፡

    3 - ከእሕራም ጀምሮ እስከ ጀምረቱል ዐቀባ ውርወራ ድረስ ተልቢያ ማስተጋባት፡፡

    4 - በእፍራድና በቅራን የአፈጻጸም ዓይነት ሐጅ ላደረገ ሰው ጠዋፉል እፋዷ ማድረግ፡፡

    5 - በጠዋፉል ቁዱም የመጀመሪያዎቹ ሦስት ዙሮች በፍጥነት መጓዝ (ረመል)፡፡

    6 - እድጥባዕ (ማደግደግ) ማለትም ከወገብ በላይ የለበሰውን ብትን ጨርቅ (ፎጣ ወይም ኩታ) ከቀኝ ብብቱ ሥር አሳልፎ ጫፎቹን ግራ ትከሻው ላይ ማድረግ፡፡

    7 - የዐረፋን ሌሊት ሚና ማደር፡፡

    8 - ጥቁሩን ድንጋይ መሳም፡፡

    9 - በሙዝደሊፋ የመግሪብና የዕሻን ሶላቶች አንድ ላይ አስቀድሞ በማጣመር መስገድ፡፡

    10 - በሙዝደሊፋ መሽዐሩል ሐራም አጠገብ ከተቻለ ከጎህ መቅደድ እስከ ፀሐይ መውጣት ድረስ መቆም ወይም መገኘት፡፡ መሽዐሩል ሐራም አጠገብ መሆን ካልተቻለ ሙዝደሊፋ በሙሉ መቆሚያ ነው፡፡

    የሐጅ ሱንና

    ከሐጅ ሱናዎች አንዱን ሱና የተወ ሰው ምንም የለበትም፣ሐጁም ትክክለኛ ነው፡፡

    የሐጅ ዋጅብ

    ከሐጅ ዋጅቦች አንዱን ዋጅብ የተው ሰው ለማካካሻ እንስሳ ማረድ ይኖርበታል፡፡