የሙስሊሞች በዓላት ሁለት ናቸው፡፡ እነሱም ዒድ አልፍጥርና ዒድ አልአድሓ ናቸው፡፡ ዒድ አልፍጥር ከረመዷን ወር ጾም በኋላ ሲሆን ዒድ አልአድሓ ደግሞ ከዐረፋ ቀን በኋላ ነው፡፡
የጃህሊይያን በዓላትና ማናቸውንም የብድዓ በዓላት አላህ በነዚህ ሁለት በዓላት ተክቶልናል፡፡ ከአነስ ብን ማሊክ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት በዘመነ ጃህሊይያ የሚጫወቱባቸው ሁለት ዓመታዊ በዓላት ነበሯቸውና ነቢዩ ﷺ ወደ መዲና ሲመጡ ፡- ‹‹የምትጫወቱባቸው ሁለት ቀናት ነበሯችሁ፣አላህ ከነሱ በላጭ በሆኑ ሁለት ቀናት በአልፍጥር ቀንና በአልአድሓ ቀን ተክቶላችኋል፡፡›› [በነሳኢ የተዘገበ]
አሉ ብለዋል፡፡ በዓላት የማንኛውም ሃይማኖት ዋነኛ መገለጫ፣ህግጋትና መርሆ በመሆናቸው፣በካፍሮች ዒድ ላይ መሳተፍና በዓላቸውን ማክበር አይፈቀድም፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹እውነቱ ከመጣልህ በኋላ ዝንባሌዎቻቸውን አትከተል፡፡ ከናንተ ለሁሉም ሕግንና መንገድን አደረግን፤›› [አል-ማኢዳህ፡48]
አላህ በዒድ ቀን የዒድ ሶላት የሚባል ሶላት ደንግጓል፤ሶላቱ ከዒዱ አበይተ መገለጫዎች አንዱ ነው፡፡
ፈርድ አልክፋያ ማለትም የወል ግዴታ ነው፡፡ ለሶላቱ በቂ የሆነ ሰው ከተገኘ ኃላፊነቱ ከተቀሩት ላይ ይነሳል፡፡ ነገሩ በጣም የጠበቀ ከመሆኑ የተነሳ ነቢዩ ﷺ እንዲሰገድ ማዘዝ ብቻ ሳይሆን ትላልቅ ሴቶችና ኮረዶችም ጭምር የማይሰግዱ የወር አበባ ያለባቸውም ሳይቀሩ ወደ መስገጃው ቦታ እንዲያመሩ አዘዋል፡፡
ይህም ሶላቱ ያለውን ትሩፋትና እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ግዴታ ስለመሆኑ ማስረጃው ፡-
1 - ‹‹ስለዚህ ለጌታህ ስገድ (በስሙ) ሠዋም፡፡›› [አል-ከውሠር፡2] የሚለው የአላህ ቃል ነው፡፡
2 - ነቢዩ ﷺ ሶላቱ እንዲሰገድ ሴቶችን ጭምር አዘዋል፡፡ ኡምሙ ዐጥይ’የህ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ፡- ‹‹የአላህ መልእክተኛﷺ በአልፍጥርና በአልአድሓ (ዒድ ሶላት)፣ለጋብቻ የደረሱና ከቤት የማይወጡ ኮረዶች፣የወር አበባ ያለባቸውንና ልጃገረዶችንም ወደ ዒድ መስገጃው ለመሄድ እንድናስወጣቸው አዘውናል፡፡ የወር አበባ ያለባቸው ከሶላቱ ገለል ብለው በመልካሙ ትእይንትና በሙስሊሞች ዱዓእ ላይ ይሳተፋሉ፣(አሉና) የአላህ መልእክተኛ ሆይ! አንዳችን የምትሸፋፈንበት ጅልባብ አይኖራትም ስላቸው እህቷ ከራሷ ጅልባብ ታልብሳት፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] አሉኝ ብለዋል፡፡
የዒድ ሶላት ወቅት ፀሐይ ወጥታ በዓይን ግምት የጦር ዘንግ ያህል ከፍ ካለችበት - የሃያ ደቂቃ ያህል ቆይታ - ጊዜ ጀምሮ ፀሐይ ከአናት አለፍ እስከምትልበት ድረስ ያለው ጊዜ ነው፡፡
ሱንናው የዒድ አልአድሓን ሶላት ለኡድህይ’ያ በቂ ጊዜ ለማግኘት ሲባል ማስቀደምና ዘካቱል ፍጥርን ለመክፈል በቂ ጊዜ እንዲኖር የዒድ አልፍጥርን ሶላት ማዘግየት ነው፡፡
የሁለቱ ዒዶች ሶላት ያለ አዘንና እቃማ ድምጽ ከፍ ተደርጎ የሚቀራበት ሁለት ረክዓ ሶላት ነው፡፡ የአሰጋገዱ ዝርዝር እንደሚከተለው ነው ፡-
1 - በመጀመሪያው ረክዓ ከእሕራም ተክቢራና ከእስትፍታሕ ዱዓእ በኋላ ከቅራኣ በፊት ሰባት ጊዜ ተክቢራ (አልሏሁ አክበር) ይላል፡፡
2 - ተዐው’ዉዝና በስመላ ካለ በኋላ ወደ ቅራኣ በመግባት ፋቲሓና አንድ ሱራ ይቀራል፡፡ ከፋቲሓ በኋላ በሁለቱ ረክዓዎች በመጀመሪያው ሱረቱል አዕላ፣በሁለተኛው ሱረቱል ጋሽያ ይቀራል፡፡ ወይም በመጀመሪያ ሱረቱ ቃፍ፣በሁለተኛው ደግሞ ሱረት አልቀመርን ያነባል፡፡
3 - በሁለተኛው ረክዓ ከመሸጋገሪያው ተክቢራ በኋላ አምስት ጊዜ ተክቢራ ያድርጋል፡፡ ትክክለኛው ከእያንዳንዱ ተክቢራ ጋር እጆችን ከፍ አለማድረግ ነው፡፡
4 - በተክቢራዎቹ ጣልቃ አላህን ያመሰግናል፣ያወድሳል፣በነቢዩ ﷺ ላይ ሶላት ያወርዳል፡፡
5 - ሶላቱን በሰላምታ ካበቃ በኋላ ወደ ምንበሩ በመውጣት ሁለት ኹጥባዎችን ያድርጋል፤በኹጥባዎቹ መካከልም ለአፍታ ይቀመጣል፡፡
6 - በሁለቱ የኹጥባው ክፍሎች በዒድ አልፍጥር ኢማሙ ከሁኔታው ጋር አግባብነት ያለውን ጉዳይ ያነሳል፡፡ በአልአድሓ ዒድ ኡድሕይ’ያን የሚመለከቱ ድንጋጌዎችንና አግባብነት ያላቸው ሌሎች ጉዳዮችን ያነሳል፡፡
ሱንናው የሁለቱን ዒዶች ሶላት በመስጊድ ሳይሆን በገላጣ መስገጃ ቦታ (ሙሰል’ላ) መስገድ ሲሆን፣አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ግን በመስጊድ ቢሰገድ ችግር የለውም፡፡
1 - ለወንድ ከአልባሳቱ ምርጡን በመልበስ አጊጦ መሄድ፤ለሴቶች ግን ያለ ጌጣጌጥና ሽቶ መሄድ፡፡
2 - ሰጋጅ ወደ ቦታው አማልዶ በመሄድ የመጀመሪያው ሶፍ ላይ መገኘት፡፡
3 - ሲሄዱ በአንድ ሲመለሱ ደግሞ በሌላ መንገድ መመለስ፡፡ ከተቻለ በእግር መጓዙ ይመረጣል፡፡ ከጃቢር (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ‹‹ነቢዩ ﷺ የዒድ ቀን ሲሆን በሌላ መንገድ ይሄዱ ነበር፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡
4 - በዒድ አልፍጥር ሶላት ከመሄድ በፊት ቁጥራቸው ኢተጋማሽ (ውትር) የሆነ (ሦስት ወይም አምስት) የተምር ፍሬዎችን መብላት፤በአልአድሓ ከሶላት እስኪመለሱ ምንም አለመቅመስ፡፡
5 - የዒድ አልፍጥርን ሶላት የዘካት አልፍጥርን ክፍያ ለመፈጸም ጊዜ ለማግኘት ማዘግየት፣የአልአድሓ ዒድ ሶላትን ደግሞ አማልዶ መስገድ፡፡
1 - ከዒድ ሶላት በፊትና በኋላ በመሰገጃ ቦታው ሱንና መስገድ የተጠላ (መክሩህ) ነው፡፡ በመስጊድ የሚሰገድ ከሆነ ግን ተሕይ’የቱል መስጅድ ይሰገዳል፡፡
2 - የዒድ ሶላት ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ያመለጠው ሰው በአሰጋገዱ መሰረት ሰግዶ መተካት ሱንና ነው፡፡ ሁለቱን ረክዓዎች ተክቢራዎቻቸውን አሟልቶ የጎደለውን ተክቶ መፈጸም ይገባል፡፡
3 - የዒድ ተክቢር አባባሉ የሚከተለው ነው፡- ‹‹አል’ሏሁ አክበር፣አል’ሏሁ አክበር፣ላእላሀ እል’ለል’ሏሁ፣ወል’ሏሁ አክበር፣አል’ሏሁ አክበሩ ወሊል’ላህል ሐምድ›› በተጨማሪም ‹‹አል’ሏሁ አክበር፣አል’ሏሁ አክበር፣አል’ሏሁ አክበሩ ከቢራ›› ማለትም ይቻላል፡፡
4 - ለወንዶች በተክቢር ድምጽን ከፍ ማድረግ ሱንና ሲሆን፣ሴት ድምጽ ዝቅ እንድታደርግ የታዘዘ ከመሆኑ አንጻር ሴቶች በተክቢር ድምጻቸውን ከፍ አያደርጉም፡፡
5 - በዒድ አልፍጥር ተክቢር የሚደረገው ከዒዱ ቀን ጎሕ መቅደድ ጀምሮ ኢማሙ ለሶላት እስከሚነሳበት ጊዜ ነው፡፡ በዒድ አልአድሓ ከዐረፋ ቀን የሱብሕ ሶላት ጀምሮ እስከ አይ’ያሙ አት’ተሸሪቅ (ከዒዱ በኋላ ያሉት ሦስት ቀናት) የመጨረሻው ቀን ጸሐይ መጥለቅ ድረስ ነው፡፡
ወደ መስገጃው ሲኬድ መንገድ ላይ፣እስኪሰገድ በተቀመጡበት ቦታ፣በጀማዓ ከሚሰገዱ የግዴታ ሶላቶች በኋላ፣በገበያ ቦታና በቤቶች . . ይደረጋል፡፡
1 - ሙስሊሞች እርስ በርሳቸው ‹‹ተቀበለል’ሏሁ ምን’ና ወምንኩም›› (ከኛና ከናንተም አላህ ይቀበለን) ›› በማለት እንኳን አደረሳችሁ መባባል የተወደደ ነው፡፡
2 - ሙስሊሞች በዒድ ቀን መደሰትና ደስታን መግለጽ፣ ዘመዶቻቸውንና ወዳጆቻቸውን እንኳን አደረሳችሁ ማለት የተወደደ ነው፡፡
3 - ዒድ የተቋረጠ ዝምድናን ለመቀጠልና የተቀያየሙትን ለማስታረቅ ልጠቀሙበት የሚገባ መልካም አጋጣሚ ነው፡፡
4 - በዒድ ዕለት መቃብሮችን መጎብኘት ያልተደነገገ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የዒድን ደስታና የመዝናኛ መንፈሱን የሚጻረር ነው፡፡
5 - በሁለቱ ዒዶች ቤተሰብና ልጆችን አላህ ሐላል ባደረጋቸው ነገሮች በአልባሳት፣በምግብና በመዝናኛዎች ማስደሰት የተደነገገ ነው፡፡ ሁለቱ ዒዶች የደስታ የፍስሐና የመዝናኛ ቀናት ናቸውና፡፡ አላህ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹፡- በአላህ ችሮታና በእዝነቱ (ይደሰቱ) በዚህም ምክንያት ይደሰቱ፤እርሱ ከሚሰበስቡት ሀብት በላጭ ነው፤በላቸው፡፡›› [ዩኑስ፡58]
6 - የሙስሊሞች የደስታና የመዝናኛ በዓላትና ድግስ ከእስላም ትምሕርቶች፣ከስነ ምግባር ሕጎቹና ከኣዳቡ ጋር የሚጻረሩ እንደ የተቃራኒ ጾታዎች መደበላለቅ (እኽትላጥ)፣የሶላት ወቅቶችን ማሳለፍ፣ሐራም የሆኑ ጨዋታ መጫወት፣ዘፈን ማየትና ማዳመጥ ወዘተ. ያሉ ነገሮችን እንዲያካትት አይፈቀድም፡፡