እሕራም

3981

   የእሕራም ትርጓሜ

የእሕራም የቋንቋ ትርጉም

መከልከል ማለት ነው፡፡

የእሕራም ሸሪዓዊ ትርጉም

ወደ ሐጅ ዕባዳ ክንውን (ኑስክ) ለመግባት ከሐጅ ተግባራት ውስጥ ካንዱ ጋር በማቀናጀት ኒያ ማድረግ ነው፡፡

  እሕራም ያለ ንይያ ሊታሰር አይችልም፡፡ ገና ከሀገሩ ሲሳፈር ሐጅ ወይም ዑምራ ለማድረግ የወሰነ በመሆኑ፣ሐጅ ወይም ዑምራ ለማድረግ በመወሰን ብቻ ሙሕሪም መሆን አይቻልም፡፡ የሐጅ ተግባራትን ወደ ማከናወን ለመግባት ንይያ ሳያደርጉ፣የተሰፉ ልብሶችን በመተው ወይም ተልቢያ (ለብበይከ አልሏሁምመ ለብበይከ) በማለት ብቻ ሙሕሪም መሆን አይቻልም፡፡ ነቢዩ ﷺ ‹‹ሥራዎች (የሚለኩት ከጀርባቸው ባለው ቁርጠኛ) ውሳኔ ነው፤እያንዳንዱ ሰውም በንይ’ያው መሰረት ነው የሚያገኘው፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

  ለእሕራም የተወደዱ ነገሮች

  1 - ገላን መታጠብ

  ኻሪጃ ብን ዘይድ ብን ሣቢት ባስተላለፉት መሰረት አባታቸው ‹‹ነቢዩ ﷺ ከተሰፉ ልብሶች ነጻ ሆነው ለእሕራም ገላቸውን መታጠባቸውን አይተዋል፡፡›› [በትርምዚ የተዘገበ]

  2 - ራስን ንጹሕና ጽዱ ማድረግ

  ይህም የብብቶችንና የብልት አካባቢን ጸጉር በማስወገድ፣ሪዝን በማሳጠርና ጥፍሮችን በመቆረጥ ነው፡፡

  3 - ሽቶ መቀባት

  ዓእሻ (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት ፡- ‹‹የአላህ መልእክተኛ ﷺ እሕራም ሲያደርጉ ለእሕራማቸው ሽቶ እቀባቸው ነበር፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

  ሙሕሪሙ ልብሱን ሽቶ ማስነካት የለበትም፡፡ የአላህ መልእክተኛ ﷺ ‹‹ከልብስ ዘዕፈራንም ሆነ ወርስ [የሽቶ መዓዛ ያለው ብጫማ ተክል ሲሆን ለመንከሪያነት ያገለግላል፡፡] የነካውን ነገር አትልበሱ፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

  ሽቶ

  4 - ወንድ ከእሕራም በፊት [የተሰፋ ልብስ ለሙሕሪም ከተከለከሉ ነገሮች አንዱ በመሆኑ ከእሕራም በኋላ ሙሉ በሙሉ ከተሰፋ ልብስ ነጻ መሆን ግዴታ ነው፡፡] ከተሰፉ ልብሶች [የተሰፋ ልብስ ማለት በአካል ልክ የተሰፋ ወይም ለሙሉ አካል የተሰፋ እንደ ሸሚዝ ቀሚስ ሱሪ ያለ ልብስ ነው፡፡] ነጻ ሆኖ ሁለት ነጫጭ ከወገብ በታች የሚታጠቅ ሽርጥና ከላይ ኩታ (ፎጣ) ከነጠላ ጫማ ጋር መልበስ

  ነቢዩ ﷺ ‹‹አንዳችሁ በሽርጥ፣በኩታና በነጠላ (ሰንደል) ጫማዎች እሕራም ያድርግ፤ነጠላ ጫማ ካላገኘ ረዥም ጫማ ለብሶ ቁርጭምጭሚቶች ላይ ይቁረጣቸው፡፡›› [በአሕመድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

  ሴት ግን ባስፈለጋት ልብስ እሕራም ማድረግ ትችላለች፡፡ የተለየ ቀለም ያለው ልብስ እንድትለብስ አትጠየቅም፡፡ በአለባበሷ ወንድን ከመምሰልና የጌጥ ልብስ ከመልበስ መራቅ ይኖርባታል፡፡ እሕራም ላይ እያለች ንቃብም (ዓይነርግብ) ሆነ የእጅ ሹራብ41 መልበስ የለባትም፡፡ ባዕድ ወንዶች በሚኖሩበት ጊዜ ግን ክንንቧን ከራሷ አወርዳ ፊቷን ትሸፍናለች፡፡

  ከዓእሻ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት ‹‹ከአላህ መልእክተኛ ﷺ ጋር በእሕራም ላይ ሆነን ተጓዦች በአጠገባችን ያልፉ የነበረ ሲሆን ከኛ ትይዩ በሚሆኑበት ጊዜ አንዳችን ክንብንቧን ከራሷ ወደ ፊቷ ታወርድና ሲያልፉ እንገልጥ ነበር፡፡›› [በአቡ ዳዉድ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

  ሽርጥና ፎጣ ለሙሕሪም ወንድ
  ነጠላ ጫማ ሙሕሪም ለሆነ ወንድ
  የእጅ ጓንቶች ሙሕሪም ለሆነች ሴት
  ንቃብ ሙሕሪም ለሆነች ሴት

  በእሕራም የተከለከሉ ነገሮች

  1 - ለወንድ ከራስ ጋር በሚነካካ ነገር ራሱን መሸፈን

  እብን ዑመር (ረዐ) ባስተላለፉት መሰረት አንድ ሰውዬ የአላህ መልእክተኛ ሆይ! አሕራም ያደረገ ሰው ከልብስ ምን ይለብሳል? ብሎ ሲጠይቅ የአላህ መልእክተኛ ﷺ ‹‹ቀሚሶችን፣የራስ ጥምጣምም፣ሱሪዎችንም ሆነ በርኖሶችን አትልበሱ፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

  በተጨማሪም ነቢዩ ﷺ እሕራም ላይ እያለ የሞተውን አገናነዝ አስመልክተው ፡- ‹‹የቅያማ ቀን ተልቢያ (ለብ’በይከ አል’ሏሁም’መ ለብ’በይከ) እያለ ይቀሰቀሳልና ራሱን አትሸፍኑ፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

  ከራስ ጋር የማይጣበቅና የማይነካካ እንደ ጃንጥላ፣ድንኳን፣የቤት ጣሪያና መኪና ያለውን መጠቀም ኃጢአት የለበትም፡፡

  የራስ ጥምጣም ለሙሕሪም ወንድ
  ሱሪ መልበስ ለሙሕሪም ወንድ
  ኮፊያ ለሙሕሪም ወንድ
  ጃንጥላ ለሙሕሪም ወንድ

  2 - ለወንድ የተሰፋ ልብስ መልበስ

  የተሰፋ ልብስ ማለት በሙሉ ገላ ወይም በከፊል ገላ ልክ የተሰፋ እንደ ሱሪ፣ቀሚስ፣ሸሚዝ፣ረዥም ጫማ፣ካልሲ፣የእጅ ሹራብ ያለው ሁሉ ነው፡፡ ይህም ‹‹ቀሚሶችን፣የራስ ጥምጣምም፣ሱሪዎችንም በርኖሶችንም ሆነ ረዥም ጫማዎችን አትልበሱ፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] በሚለው የላይኛው የእብን ዑመር ሐዲስ መሰረት ነው፡፡

  እሕራም ማድረግ የፈለገ ሰው ሽርጥ ካላገኘ ሽርጥ [የእሕራም ልብሱን ሻንጣው ውስጥ አይሮፕላን ላይ ወይም መርከብ ላይ የረሳ ሰው፣ልብሶቹን አውልቆ ሱሪውን እንደለበሰ እሕራም ማድረግና ሸሚዙን እንደ ኩታ ከወገቡ በላይ መጠምጠም ይችላል፡፡ ወደ ወደብ ሲደርስ የእሕራም ልብሱን አውጥቶ ይለብሳል፡፡] እስኪያገኝ ድረስ ሱሪ መልበስ ይችላል፤ነጠላ ጫማ ማግኘት ካልቻለም ሽፍን ጫማ መልበስ ይችላል፡፡ ነቢዩ ﷺ ‹‹ነጠላ ጫማ ካላገኘ ረዥም ጫማ ለብሶ ቁርጭምጭሚቶች ላይ ይቁረጣቸው፡፡›› [በእብን ኹዘይማ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

  የተሰፋ ልብስ መልበስ ለሙሕሪም ወንድ
  ሽፍን ጫማ
  ረዥም ጫማ ለሙሕሪም ወንድ

  3 - የየብስ እንስሳን መግደል ወይም ማደን

  አላህ እንዲህ ብሏል ፡- ‹‹በሐጅ ሥራ ውስጥ ስትኾኑ አውሬን አትግደሉ፤›› [አል-ማኢዳህ:95] ይህም በሐጅና በዑምራ እሕራም ውስጥ እያላችሁ ማለት ነው፡፡

  በተጨማሪም አላህ እንዲህ ብሏል ፡- ‹‹በሐጅም ላይ እስካላችሁ ድረስ የየብስ አውሬ በናንተ ላይ እርም ተደረገ፤›› [አል-ማኢዳህ:96] የየብስ አውሬ ማለት ለማዳ ያልሆኑና የሚበሉ የሆኑ እንስሳትና አዕዋፍ ናቸው፡፡

  የቤት ለማዳ እንስሳት ግን አደን አይደሉምና ዶሮ፣የቤት እንስሳትና የማሳሰሉትን ማረድ ለሙሕሪሙ የተፈቀደ ነው፡፡ የባሕር አደንም የተፈቀደ ነው፡፡ አላህ እንዲህ ብሏልና ፡- ‹‹የባሕር ታዳኝና ምግቡ . . . ለናንተ ተፈቀደ፤›› [አል-ማኢዳህ:96]

  እንደ እባብና ጊንጥ ያሉ የማይበሉ ሐራም የሆኑ እንስሳትን መግደል የተፈቀደ ነው፡፡ ከመግደል ውጭ መከላከል የሚችልበት ሌላ መንገድ ከሌለው ሙሕሪሙ የተተናኮለውን ማንኛውንም እንስሳ መግደል ይፈቀድለታል፡፡

  ጊንጥ
  የባሕር አደን ማደን (ማጥመድ) ለሙሕሪም የተፈቀደ ነው
  የየብስ አዕዋፍን ማደን
  እባብ
  የቤት እንስሳትን ማረድ ይፈቀዳል

  4 - ጸጉርን መላጨት፣ማሳጠር ወይም መንጨት

  አላህ እንዲህ ብሏል ፡- ‹‹ሀድዩም (የሚሰዋው እንስሳ) እስፍራው እስከሚደርስ ድረስ ራሶቻችሁን አትላጩ፤››

  [አል-ማኢዳህ:95]

  እገዳው ከራስ ጸጉር ጋር በንጽጽሮሽ ሁሉንም የገላ ጸጉር ያጠቃልላል፡፡

  ጸጉር መላጨትና ማሳጠር

  5 - ጥፍር መቆረጥ

  የእጅና የእግር ጥፍሮችን መቆረጥ ነው፡፡

  የእግር ጥፍሮችን መቆረጥ
  የእጅ ጥፍሮችን መቆረጥ

  6 - የሽቶ ገላና ልብስን መንካት

  ወደ እሕራም ከገቡ በኋላ ገላን ወይም ልብስን ሽቶ መቀባት ወይም ለማሽተት ዓላማ መጠቀም የተከለከለ ነው፡፡ ይህም ቀደም ሲል በቀረበውና ‹‹ከልብስ ዘዕፈራንም ሆነ ወርስ የነካውን ነገር አትልበሱ፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ]

  በሚለው የእብን ዑመር (ረዐ) ሐዲስ መሰረት ነው፡፡ በተጨማሪም በሐጅ ላይ እያለ የሞተውን ሰውዬ አገናነዝ አስመልክተው ነቢዩ ﷺ ‹‹በሽቶ አታጥኑት›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

  ለሙሕሪም ሰው ገላን ሽቶ ማስነካት
  ለሙሕሪም ሰው ልብስን ሽቶ ማስነካት

  7 - ንካህ (የጋብቻ ውል) ማሰር

  ከዑሥማን (ረዐ) በተላለፈው መሰረት የአላህ መልእክተኛ ﷺ ‹‹እሕራም ላይ ያለ ሰው ለራሱ ንካሕ አያስርም፤ ለሌላ ሰውም አይድርም፤አያጭምም፡፡›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

  8 - የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸም

  አላህ እንዲህ ብሏል ፡- ‹‹በነርሱም ውስጥ ሐጅን (እንዲሠራ) ነፍሱን ያስገደደ ሰው፣በሐጅ ውስጥ ሴትን መገናኘት፣ . . የለም፤›› [አል-በቀራህ:195]

  እብን ዐባስ (ረዐ) እንዳሉት ሴትን መገናኘት ማለት ‹‹ወሲባዊ ተራክቦ መፈጸም›› ማለት ሲሆን ይህም ከእሕራም እገዳዎች ውስጥ እጅግ የጠበቀ እገዳ ነው፡፡

  9 - ከተቃራኒ ጾታ ጋር ከማህጸን አፍ ውጭ ገላ ለገላ መነካካት

  ይህ በሐጅ ላይ ሐራም ወደ ሆነው የግብረ ሥጋ ግንኙነት መረማመጃ ስለሆኑ እንደ መሳሳምና መተሻሸት ያሉትን የሚያጠቃልል ነው፡፡

  ሴትን የሚመለከቱ በእሕራም የተከለከሉ ነገሮች

  በእሕራም እገዳዎች ላይ ሴት እንደ ወንዱ ስትሆን በሚከተሉት ብቻ ከወንድ ትለያለች

  1- የተሰፋ ልብስ ትለብሳለች

  2- ራሷን ትሸፍናለች

  3- ንቃበም ሆነ የእጅ ሹራብ (ጓንት) አትለብስም፡፡ ነቢዩ ﷺ ‹‹እሕራም ላይ ያለች ሴት ንቃብ አትለብስም፤የእጅ ሹራቦችም አታደርግም፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋልና፡፡

  ባእድ በሆኑ ወንዶች ፊት ሴቷ በንቃብ ሳይሆን ክንብንቧን ከራሷ በማውረድ ፊቷን ትሸፍናለች፡፡ የወርቅ ጊጥ መልበስም ይፈቀድላታል፡፡

  መመሪያዎች

  1 - ሁለት ረክዓ የእሕራም ሱና የሚባል ሶላት ምንም መሰረት የለውም፤እሕራም በሚደረግበት ጊዜ የተለየ ዓይነት ዱዓእ ማድረግም አልተደነገገም፡

  2 - መንገደኛው በአይሮፕላን የሚጓዝ ሆኖ ሚቃቱ ዘንድ ሲደርስ የእሕራም ልብስ መልበስ አይመቸኝም የሚል ስጋት ካደረበት ከቤቱ ወይም ከአይሮፕላን ማረፊያው ጀምሮ መልበስ ይችላል፡፡ ከሚቃቱ ትይዩ ከመድረሱ በፊት እሕራም ሳያደርግ በልብሱ ብቻ ሙሕሪም አይሆንም፡፡

  3 - አንዳንድ ሐጃጆች የእሕራም ልብስ በመልበሳቸው ብቻ የቀኝ ትከሻቸውን በመግለጥ ያራቁታሉ፤ይህም ‹‹እድጥባዕ›› (ማደግደግ) በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ይህ ትክክለኛ አድራጎት አይደለም፡፡ እድጥባዕ የሚደረገው በጠዋፍ አልቁዱም ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ትከሻዎች ይሸፈናሉ፡፡

  እድጥባዕ

  አጠቃላይ ምክር ለሐጃጆች

  አንድ ሙስሊም ለሐጅ ወይም ለዑምራ መጓዝ ከወሰነ የሚከተሉትን መመሪያዎች መከተል ግዴታ ይሆንበታል፡-

  1 - ቤተሰቡንና ወዳጆቹን ያዘዘውን በመፈጸም እና ከከለከለው በመታቀብ አላህን ይፈሩት ዘንድ መምከርና ማሳሰብ፡፡

  2 - በሰው ላይ ያለውን እዳና ሌሎች በርሱ ላይ ያላቸውን ዕዳ በምስክሮች ፊት በጽሑፍ ማስፈር፡፡

  3 - ከሁሉም ዓይነት ኃጢአት ፍጹማዊ የሆነ ተውበት አድርጎ ወደ አላህ መመለስ፡፡ እናንተ ምእመናን ሆይ! ትድኑ ዘንድ ሁላችሁም በመጸጸት ወደ አላህ ተመለሱ፡፡ አላህ እንዲህ ብሏልና ፡- ‹‹እላንተ ያመናችሁ ሆይ! ንጹሕ የኾነችን ጸጸት በመጸጸት ወደ አላህ ተመለሱ፤ጌታችሁ ከናንተ ኃጢአቶቻችሁን ሊሰርይላችሁ፣ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸውንም ገነቶች ሊያስገባችሁ ይከጀላልና፤›› [አል-ተሕሪም:8]

  4 - በነፍስ በገንዘብ ወይም በክብር ጥሰት ሌሎችን የበደለበት ነገር (መዛሊም) ካለበት ከመጓዙ በፊት የሚከፈለውን መክፈልና ይቅርታቸውን ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ነቢዩ ﷺ ‹‹በገንዘብ ወይም በክብር ጥሰት ወንድሙን የበደለበት ነገር ያለበት ሰው ምንም ዲናርም ሆነ ድርሃም የማይኖርበት ጊዜ ከመምጣቱ በፊት ዛሬውኑ ራሱን ነጻ ያድርግ፤መልካም ሥራ ካለው በፈጸመው በደል መጠን ይወስድበታል፣በጎ ሥራዎች ከሌሉት ደግሞ ከበደለው ሰውዬ ኃጢአቶቹ ተወስደው በርሱ ላይ ይጫናለ፡፡›› [በቡኻሪ የተዘገበ] ብለዋል፡፡

  5 - ለሐጅና ዑምራው ሐላል ከሆነ ምንጭ የተገኘ ንጹሕ ገንዘብ መምረጥ፡፡ ነቢዩ ﷺ ‹‹አላህ መልካም ነውና መልካም የሆነውን እንጂ አይቀበልም፤አላህ ምእመናንን ‹እናንተ መልእክተኞች ሆይ! ከመልካሙ ነገር ብሉ፣በጎውንም ሥሩ› በማለት መልእክተኞችን ባዘዘበት ነገር፣ ‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ከሰጠናችሁ መልካም ሲሳይ ብሉ፤አላህንም እርሱን ብቻ የምትገዙት እንደ ሆናችሁ አመስግኑ፡፡› በማለት አዟቸዋል፡ ረዥም መንገድ ተሳፍሮ ጸጉሩ ተንጫርሮና በአቧራ ተውጦ ‹ጌታዬ ! ጌታዬ! እያለ እጆቹን ወደ ሰማይ (በዱዓእ) ይዘረጋል፣ምግቡ ሐራም፣መጠጡ ሐራም፣የሚለብሰው ሐራም፣በሐራም የተቀለበ እየሆነ የዚህ ዓይነቱ ሰው (ዱዓእ) እንዴት ተቀባይነት ያገኛል?!›› [በሙስሊም የተዘገበ] ብለዋል፡፡

  6 - ሐጅና ዑምራውን ለአላህና ለኣኽራው የታሰበ፣በነዚያ ቅዱሳን ቦታዎች በአንደበትና በተግባር የሚፈጽማቸውን ሁሉ የአላህን ውዴታ ለማግኘትና ወደርሱ ለመቅረብ የታለመ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ በሐጁ ዓለማዊ ጥቅም ወይም ታይታን ወይም ዝናንና ከሌሎች በልጦ መታየትን ከመፈለግ ዓላማ በእጅጉ መጠንቀቅ ይገባዋል፡፡

  7 - ሐጅና ዑምራን አስመልክቶ የተደነገገለትን ነገር መማር፣ሕግጋትና ደንቦቹን መረዳትና መገንዘብ፣የማያውቀውን ነገር መጠየቅና የተሟላ ዕውቀትና መረጃ ማግኘት ይኖርበታል፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ብዙዎቹ ሐጃጆች ስለ ሐጅ ሥርዓት አፈጻጸም ምንም ዕውቀት ሳይኖራቸው ወደ ሐጅ የሚሄዱ በመሆናቸው ሐጃቸውን በሚያበላሽ ሁኔታ አንዳንድ የሐጅ ግዴታዎች ሲያመልጣቸው ይስተዋላሉ፡፡

  እሕራምን ከሚመለከቱ ድንጋጌዎች

  እሕራም ላይ የሚገኝ ሰው በዉዱእ ወይም በገላ ትጥበት ጊዜ ጥቂት ጸጉሮች ቢወድቁ ከሪዙ፣ከጺሙም ሆነ ከጥፍሩ የሚወድቅ ነገር ቢኖር ሆን ብሎ እስካላደረገ ድረስ ችግር የለውም፡፡ በዚህ ወንድና ሴት አንድ ሲሆኑ ከጸጉሯ ወይም ከጥፍሯ የሚወድቅ ነገር ቢኖር ችግር አይፈጥርባትም፡፡ ሙሕሪሙ አስፈላጊ ከሆነ ወይም የሚጠቅመው ከሆነ እግሩ ላይ ማሰሪያ ማድረግ ይፈቀድለታል፡፡

  - ቅድመ ሁኔታ በንይያ:-

  በሽታ ያለበት ሰው ወይም የሐጅ ክንውኑን ከማሟላት የሚያግደው ነገር ይኖራል ብሎ ከሰጋ እሕራም በሚያደርግበት ጊዜ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ‹‹አላህ ሆይ! ለዑምራ (ለሐጅ) ጥሪህን ተቀብያለሁ! (ለብበይከ አልሏሁምመ ብዑምረትን) የሚያሰናክለኝ ነገር ከተከሰተ ከእሕራም የምወጣው በተሰናከልኩበት ቦታ ነው፡፡›› ማለት ይችላል፡ ከዓእሻ (ረዐ) በተላለፈው መሰረት የአላህ መልእክተኛ ﷺ ወደ ዱባዓ ብንት ዙበይር ሄደው ‹‹ሐጅ ማድረግ ፈልግሽ ይሆን?›› ሲሉ ‹‹ወላሂ ሕመም ተሰምቶኛል እንጂ›› አሏቸው፡፡ እሳቸውም ‹አላህ ሆይ! ከእሕራሜ የምወጣው በያዝከኝ ቦታ ላይ ነው ብለሽ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጭና ሐጅ አድርጊ፡፡›› [በቡኻሪና ሙስሊም የተዘገበ] አሉ ብለዋል፡፡